በክልሉ 9 ወራት 77 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል፦ አቶ ግዛው ጋግያብ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ የ9 ወራት የተግባር አፈጻጸም ግምገማ አድርጓል ።

ባለፉት 9 ወራቶች ከፈጻሚ ዝግጅት ጀምሮ በቢሮው የተሰጡ ተልዕኮዎችን በብቃት ለመወጣት እንዲያስችል ዘርፈ ብዙ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን የቢሮ ኃላፊው አቶ ግዛው ጋግያብ ተናግረዋል ።

ቢሮው በአይሲቲ እና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች በተጠናቀቀው 9 ወራቶች በዋና ዋና ተግባራት የተሻሉ ስራዎች መከናወናቸውንም ገልጸዋል ።

የኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ ኃላፊው አቶ ግዛው ጋግያብ እንደተናገሩት ከተከናወኑ ተግባራት ውስጥ ነባር ኢንዱስትሪዎችን ማጠናከርና አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች እንዲፈጠሩ የማድረግ ስራዎች ዋነኛ ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ከ77 በላይ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን በ 9 ወራት ውስጥ በመፍጠር ከ776 በላይ ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ተደርጓል ሲሉም ተናግረዋል ።

ከዚህ ቀደም ከነበረው ላይ አዳዲስ ኢንዱትሪዎችን በመፍጠር አሁን ላይ በክልሉ 777 ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን አቶ ግዛው አብራርተዋል ።

ኢንዱስትሪዎች ብቃት ኖሯቸው ጥራትና ተኪ ምርቶችን አምርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑም የተጠናከረ የድጋፍና ክትትል ስራዎች መከናወናቸውንም አቶ ግዛው አስረድተዋል ።

ኢንዱስትሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የፋይናንስ ድጋፍ ከልማት ባንክና ከደቡብ ግሎባል ጋር በመተባበር ከ33.3 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የዕቃ ሊዝ ድጋፍ ተደርጎ 77 ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ መግባት ችለዋል ሲሉም ተናግረዋል ።

በክልሉ ለ184 ኢንዲስትሪያሊስቶች ከ71.5 ሚሊዮን ብር በላይ የሀገረ ውስጥ የገበያ ትስስር መፈጠር መቻሉንም አቶ ግዛው አብራርተዋል ።

በተፈጠረው የገበያ ትስስር ከክልሉ 3 ኢንዱስትሪዎች ከውጭ ሀገራት ጋር የገበያ ትስስር እንደተፈጠረላቸውም ኃላፊው አብራርተዋል ።

ኢንዱስትሪያሊስቶች ውጤታማ እንዳይሆኑ ማነቆ የሆኑ የብድር ስርጭት ችግር፣የመብራት፣የገበያ ትስስርና መሰል ችግሮችን በመለየትና በመቅረፍ ተጠቃሚነታቸውን ከፍ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራልም ብለዋል።

ለዚህም ቢሮው የኢንዱስትሪያሊስቶችን የገበያ ትስስር ችግሮችን ለመቅረፍ በሚዛን አማን ከተማ የኤግዚቢሽን እና ባዛር ዝግጅት ከነገ ጀምሮ የሚከፈት መሆኑንም አቶ ግዛው አብራርተዋል ።

በገጠር አርሶአደሮች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን የጠር ኢንዱስትሪ ስራዎችን እውን በማድረግ የአካባቢ ጸጋዎችን ወደ ዕድል ቀይረው እንዲጠቀሙ ለማስቻል ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራም ኃላፊው ጠቁመዋል።

የ5 ሚሊዮን ኢትዮ ኮደርስ ስልጠናን ተግባራዊ ከማድረግም አንጻር በክልሉ ከ8 ሺህ በላይ ዜጎች ተመዝግበው ስልጠና እየወሰዱ እንደሚገኙም አስረድተዋል።

የዲጂታል መታወቂያ(ፋይዳ) አስፈላጊነትና ጠቀሜታን ሁሉም ዜጎች በመረዳት በክልሉ የተጀመረው ይህ ስራ ውጤታማ እንዲሆንም ከክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ግዛው አብራርተዋል።

የኢንዱስትሪ እና ኢኖቬሽን ቢሮ የ9 ወራት የስራ አፈጻጸም ግምገማ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በሚዛን አማን ከተማ አድርጓል ።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *