




በብሔራዊ የገጠር መሬት መረጃ ስርዓት ላይ ያተኮረ ስልጠና ለመሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ባለሙያዎች እየተሰጠ ነው።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ በመሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ዘርፍ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ነው።
ቢሮው በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀምን ተግባራዊ ለማድረግ በክልሉ ጸድቆ ስራ ላይ የዋለውን አዋጅ መሠረት በማድረግ ወደ ስራ ከገባ ቆይቷል።
በዚህም የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀምን ውጤታማ ለማድረግ አንደኛ ዙርና ሁለተኛ ዙር ልክቶሽ አከናውኗል ።
ይህንን መረጃ ተጨባጭ ለማድረግና ከግጭትና ክርክር ነጻ በሆነ መንገድ ለማስተዳደር እንዲያስችል የብሔራዊ የገጠር መሬት መረጃ ስርዓት እውን ማድረግ ማስፈለጉን በክልሉ ግብርና ቢሮ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ አበበ ታፈሰ ተናግረዋል ።
በስልጠናው ላይ ከክልሉ ዞኖችና ከ6 ወረዳዎች የተውጣጡ ከ50 በላይ ባለሙያዎች መሳተፋቸውንም አቶ አበበ ተናግረዋል ።
ስልጠናው በንድፈ ሀሳብና በቴክኖሎጂ ታግዞ እየተሰጠ ሲሆን ባለሙያዎች ክህሎቶቻቸውን በማሳደግ ዘመናዊ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መረጃን እውን እንዲያደርጉ ያግዛልም ብለዋል።
የብሔራዊ የገጠር መሬት መረጃ ስርዓት ይስተዋል የነበረውን የድንበር ላይ ጭቅጭቅ ፣ግጭት እና የአገልግሎት ጥራት ጉድለትን በመቅረፍ የአርሶአደሩንኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የባለቤትነትን መብት ያስከብርላቸዋል ሲሉም አቶ አበበ ተናግረዋል ።
በስልጠናው ተሳታፊ ከሆኑት መካከል አቶ ሀብታሙ ታከለ ከጨና ወረዳ የመጡ ሲሆን በብሔራዊ የገጠር መሬት መረጃ ስርአት ቋት ከዚህ ቀደም የተለኩ መሬት ነክ መረጃዎችን ማስቀመጥ ቀልጣፋ አገልግሎት ከመስጠቱም ባለፈ መረጃዎች ለረጂም ዓመታት ሳይበላሹ እንዲቆዩ ያደርጋል ብለዋል።
ከኮንታ ዞን ኤላ ሀንቻኖ ወረዳ የመጡት ወ/ሪት ውባለም ባረና በበኩላቸው የብሔራዊ የገጠር መሬት መረጃ ስርአት መዘርጋቱ የአርሶአደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከፍ ያደርጋል ብለዋል።
በዘመናዊ የመረጃ ቋት የተመዘገቡ መሬቶች መንግስት ከዘርፉ መጠቀሚያ ለሚሰበሰበው ገቢ ትክክልኛ መረጃ በመሆንም ያገለግላል ሲሉ ወ/ሪት ውባለም ተናግረዋል ።
በብሔራዊ የገጠር መሬት መረጃ ስርዓት ስልጠና በቴክኖሎጂ ታግዞ እየተሰጠ መሆኑ የባለሙያዎችን ክህሎት ያሳድጋልም ተብሏል።
