በበጀት ዓመቱ የገጠር የጤና ትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎች በተሟላ መልኩ መፈጸም እንደሚገባ ተገለጸ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፣ የጤና ቢሮ “ዘላቂ እንቨስትመንት እና ፈጠራ ለጤናው ዘርፍ እምርታ” በሚል መርህ ቃል ያዘጋጀው የጤና ሴክተር ጉባኤ በታርጫ ከተማ ተካሂዷል።

ለጤናው ዘርፍ ውጤታማነት ብቃት ያለውን የአመራር ስርዓት መፈጠር እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

የጤናውን ዘርፍ ተልዕኮ በተሻለ መልኩ ለማሳካት የዘርፉ አመራር የተግባር ቁርጠኝነት መጠናከር እንዳለበት ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በበጀት ዓመቱ የገጠር የጤና ትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎች በተሟላ መልኩ መፈጸም ይገባል ብለዋል።

የህዝብ የልማት አቅሞች በማቀናጀት በእያንዳንዱ ቀበሌ የጤና ኬላዎች በመገንባት የጤና አግልግሎት ተደራሽነትን ማስፋት እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

በሚቀጥሉት አጭር ጊዜ ውስጥ የማዐጤመ አዲስ አባላት ማፍራትና የዕድሳት ተግባር በልዩ ትኩረት መከናወን እንዳለበት ያስገነዘቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በየደረጃው የሚገኝ አመራር በየዘርፉ የሚቆጠር ውጤት ማስመዝገብ አለበት ብለዋል።

በወልድ ጊዜ የሚከሰተውኝ የእናቶች ሞት ለመቀነስ የጤና ተቋማት ራሳቸውን ፈትሽው ችግሮችን በመለየት መፍተሔ ማበጀት እንዳለባቸውም በአጽንኦት ተናግረዋል።

የመድኃኒት አቅርቦት በማሳለጥ፣ዜጎች ተገቢውን የህክምና አግልግሎት እንዲያገኙ ማስቻል እንደሚገባ ያስገነዘቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ወርደው መደገፍና ማብቃት ከአመራሩ ይጠበቃል ብለዋል።

የኤክስቴንሽን ፕሮግራም ውጤታማነት በመገምገም ተገቢውን አግልግሎት እንዲሰጡ መደገፍና የተጠያቂነት አሰራር መዘርጋት እንደሚገባ ነው የክልሉ የጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም የገለጹት።

የጤና ኬላ ግንባታዎች በጤና ሚኒስቴር ወጥ መለኪያ መሠረት ብቻ መሆን እንዳለበት ያስገነዘቡት አቶ ኢብራሂም በጤና ተቋማት ግንባታና ግብዓት ማሟላት ላይ ኅብረተሰቡን ማሳተፍ ይገባል ብለዋል።

በገጠር ተገቢውን የጤና አግልግሎት ተደራሽ ከማድረግ አኳያ በጤና ኤክስቴንሽን ስርዓት ላይ የሚስተዋለውን ተተክለው ያለመሥራት ችግር መቅረፍና የተጠያቂነት ስርዓት ማስፈን እንደሚገባ ነው የመድረኩ ተሳታፊዎች የጠየቁት።

በገጠር ትራንስፎርሜሽን የጤና አጀንዳዎችን በበጀት ዓመቱ በተሻለ መልኩ ለመፈጸም ቁርጠኛ እንደሆኑ የገለጹት ተሳታፊዎቹ፥ የጤና ተቋማት ለአግልግሎት ምቹ ለማድረግ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

እናቶች በጤና ተቋም እንዲወልዱ በማስቻል የእናቶችና የህጻናት ሞትን ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ በትኩረት እንደሚሰሩም ቁርጠኝነታቸውን ገልጸዋል።

በመድረኩ በጤናው ዘርፍ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ተቋማትና ግለሰቦች የዋናጫና የእውቅና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *