ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ግጭቶችንና አለመግባባቶችን በእርቅ በመፍታት ፍትህን አስጠብቆ ለማየቆት የጎላ ሚና እንዳላቸው ተገለጸ

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት ባህላዊ ፍርድ ቤቶቹን በአዋጅ ቁጥር 35/2016 መሠረት በማቋቋም በሁሉም ወረዳዎችና ቀበሌዎች አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ለዚህም በክልሉ በምዕራብ ኦሞ ዞን በመኤኒት ጎልዲያ ወረዳ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ባህላዊ ፍርድ ቤቶቹ እስከ ቀበሌ ድረስ በማቋቋም ተግባራዊ በማድረግ ወደ ስራ ተገብቶ ውጤት ተመዝግቧል፡፡

በወረዳው ያነጋገርናቸው አንዳንድ ባህላዊ ፍርድ ቤት አካላት እንደገለጹት፣ ባህላዊ ፍርድ ቤት እውነትን ከመግለጥ አንፃር ህብረተሰቡ የርቀት መንገድ ተጉዞ ሳይጉላለ በአቅራቢያው ትክክለኛ ፍትህ እንዲያገኝ ወደ በባህላዊ መንገድ የማስታረቅ ስራ በሰፊው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመኤኒት ጎልዲያ ወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ብዙአየሁ ኬላጌ፤ ዜጎች በአቅራቢያቸው ፍትህ እንዲያገኙ በተለይም የባህል እሴቶችን አውቀው እና ጠብቀው እንዲሄዱ ከማድረግ አንፃር ባህላዊ ፍርድ ቤቶች የጎላ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል፡

ለዚህም በወረዳው ካሉት ከ17 መዋቅሮች በ11 ቀበሌዎች ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን በማቋቋም በአካባቢ ተቀባይነት ባላቸው የሀገር ሽማግሌዎች በመፍታት ችግሩ በአጭሩ በመቋጨት እውነትና ፍትህ እንዳይደበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ነው የገለፁት፡፡

ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ማህበረሰቡ ባህልና ወጉን ጠብቆ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን በእርቅ በመፍታት ፍትህን አስጠብቆ ለማየቆት የሚያስችል በመሆኑ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ይበልጥ እንዲጠናከር አቶ ብዙአየሁ ኬላጌ አሳስበዋል፡፡

የመኤኒት ጎልዲያ ወረዳ ዋና አስተዳደር አቶ ጎንጥዮ ፋጂዮ፤ ማህበረሰቡን በማሳተፍ በወረዳ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች መቋቋማቸውን ገልጸው ይህንንም በማስፋፋትና በማጠናከር ህብረተሰቡ ፍትህን ፍለጋ እንዳይጉላላና ለከፍተኛ ወጪ እንዳይዳረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በዚህም ግጭቶችን ተፈተው ማህበረሰቡ በአቅራቢያው ፍትህ እንዲያገኝ በማድረግ ሰላም እንዲያረጋግጥ ምቹ አካባቢ መፍጠራቸውን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ የተጀመረው ግንዛቤ የመፍጠር፣ በሰው ሀይልና በበጀት በመደገፍ ስራ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *