




በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ማህበራዊ ልማት፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የተከሰተውን ከፍተኛ የወባ ወረርሽኝ ለመከላከል ሁለንተናዊ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።
ቋሚ ኮሚቴው በክልሉ በከፋ እና በዳውሮ ዞኖች የወባ ወረርሽኙን አስመልክቶ የመስክ ጉብኝት አድርጓል።
ቋሚ ኮሚቴው በካፋ ዞን በገብረፃዲቅ ሻዎ ጠቅላላ ሆስፒታል፣ በጎጀብ ጤና ጣቢያ እና በሾንባ ቅጭብ ጤና ኬላ ጉብኝት ባደረገበት ወቅት ወረርሽኙ በህዝቡ ላይ ተጽዕኖ ቢያሳድርም ችግሩን ለመከላከል ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።
በካፋ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች የወባ ወረርሽኙን ለመከላከል ውሃማ አካላትን የማፋሰስና የማዳፈን ስራ ቢከናወንም፤የኬሚካል ርጭት በአቅርቦት ችግር በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ሊሆን አለመቻሉን ቋሚ ኮሚቴው አረጋግጧል።
የቋሚ ኮሚቴው አባልና የቡድኑ አስተባባሪ የተከበሩ ወ/ሮ አሚራ አህመድ በካፋ እና በዳውሮ ዞኖች ጤና ተቋማት በጀትን ጨምሮ የወባ መከላከያ ግብዓቶች አጥረት ሊቀረፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የካፋ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አክሊሉ አሰፋ የወረርሽኙን አሳሳቢነት ገልጸው፤ በኬሚካል እጥረት ምክንያት እስካሁን የቤት ለቤት ርጭት መካሄድ የተቻለው በሁለት ወረዳዎች ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።
የገብረፃዲቅ ሻዎ አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቅረማሪያም ጳውሎስ በበኩላቸው አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የወባ ስርጭቱ እየጨመረ ቢሆንም የሞት መጠን እየቀነሰ መሆኑን ለቋሚ ኮሚቴው ገልጸዋል።
በየቀኑ በወባ በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር የተለያየ መሆኑን የገለፁት ስራ አስኪያጁ፤ በሌላ በኩል የህክምና ግብዓት፣ የመድሀኒት እና የደም አቅርቦት ችግሮች መኖራቸውን ተናግረዋል።
በተመሳሳይም ኮሚቴው በዳውሮ ዞን ታርጫ አጠቃላይ ሆስፒታል እና የዛባ ጋዞ ቃራዎ ጤና ጣቢያ ባደረገው የመስክ ጉብኝት የወባ ወረርሽኝ ስርጭቱ ከባለፉት ወራቶች አንጻር እየቀነሰ መምጣቱን ተገንዝቧል።
የታርጫ አጠቃላይ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ያዕቆብ ሌንጫ ባለፉት ወራት የወባ ስርጭቱ የከፋ እንደነበር ገልጸው፤ አሁን ላይ ወረርሽኙን ለመግታት ህዝብን ያሳተፈ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።
የሆስፒታሉ የኦክስጅን ፕላንት አለመኖር፣ የበጀት እና የተኝቶ ህክምና አልጋ እጥረት ማነቆ ችግሮች መሆናቸውን ለቋሚ ኮሚቴው አንስተዋል።
የጉብኝቱ አስተባባሪ የተከበሩ ወ/ሮ አሚራ አህመድ የወባ ወረርሽኙን በመከላከል ረገድ አላሰራ ያሉ ችግሮች እንዲቀረፉ ኮሚቴው ከጤና ሚንስቴር ጋር ተወያይቶ የመፍትሔ አቅጣጫ የሚቀመጥ መሆኑን ማስገንዘባቸዉን የህብዝ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመለክታል።
