የህዝባችንን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ውጤት ተኮር አመራር እንገነባለን፦ አቶ ወንድሙ ኩርታ

Spread the love

በቤንች ሸኮ ዞን ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የፓርቲና የመንግስት ተግባራት አፈፃፀም ግምገማ እና የአመራር ምዘና መድረክ በተቀመጡ አቅጣጫዎች ላይ መግባባት በመፍጠር በስኬት ተጠናቀቀ።

በመድረኩ የዞኑ የግማሽ ዓመት የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ በአመራሮች መካከል ጥልቅ ውይይት ተካሂዷል።

ባለፉት ስድስት ወራት በተለያዩ ዘርፎች የተመዘገቡ አዎንታዊ ውጤቶች እንዲቀጥሉ ጎልተው የታዩ ክፍተቶች ደግሞ በፍጥነት እንዲታረሙ አቅጣጫ ተቀምጧል።

በመድረኩ እያንዳንዱ አመራር በአመለካከት ጥራት፣ በአመራር ኃላፊነት አፈፃፀም፣ በስብዕናና በስነ-ምግባር እንዲሁም የፓርቲ ተልዕኮዎችን በመፈፀም አንፃር በሂስና ግለ-ሂስ ተገምግሟል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት አመራሩ ከመደበኛ አሰራር በላይ በመውጣት ችግር ፈቺ አመራር መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

በተቋማት ውስጥ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በቁርጠኝነት መፍታትና ተቋማትን ማጥራት አስፈላጊ ነው ያሉት አፈጉ ባኤው ይህ የግምገማ መድረክ ተግባራዊ ውጤት ሊያመጣ የሚችል መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በዞኑ የስራ ዕድል ፈጠራና የመንግስት ኢኒሼቲቮች በተቀናጀ አሰራር መፈፀም እንደሚገባ አሳስበዋል።

የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ከበደ በበኩላቸው ዞኑ ዋጋ ከፍሎ ያረጋገጠውን ሰላም ወደ ልማት መቀየር እንደሚገባ ጠቅሰው ህገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን በቁርጠኝነት መታገል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በተቋማት ውስጥ የሚታይ ብልሹ አሰራር ላይ እርምጃ ከመውሰድ ባለፈ ውጤት ተኮር አሰራር መጠናከር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን በበኩላቸው በዞኑ የተመዘገቡ ውጤቶች ለመሳካት የአመራሩ አንድነት ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል። ሆኖም ከፓርቲው የተቀመጡ ግቦች አንፃር ገና ብዙ ስራዎች እንደሚቀር ጠቁመዋል።

አያይዘውም ተቋማት ከታችኛው መዋቅር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር፣ በተቋማት ውስጥ ያሉ ባለሙያዎችን እና የአገልግሎት አሰጣጥን ማጥራት እንዲሁም አመራሩ ከግል ጥቅም ይልቅ የህዝብን ጥቅም ማስቀደም እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

በመድረኩ ማጠቃለያ ለቀጣይ ስድስት ወራት ትኩረት የሚሹ ዋና ዋና የስራ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መድረኩ ተጠናቋል ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *