




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን በምዕራብ ኦሞ ዞን፣ ቤሮ ወረዳ የብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ግንባታ የመሠረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል።
በመርሐግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ፍቅሬ፥ የክልሉ መንግሥት በአርብቶአደሩ ቀጠና ዘላቂ ሠላም በማስፈን ልማት ለማምጣት በልዩ ትኩረት እየሰራ መኾኑን ተናግረዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ለማዕድን ዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት፣ የፖሊሲ ማሻሻያ እና ዕሳቤ የቢሮ ወረዳም ከዘርፉ ልማት ተጠቃሚ መኾን መጀመሯን አቶ ፍቅሬ የገለጹት።
የማዕድን ሀብት በባህሪው አላቂ በመኾኑ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ወደ ሌሎች ልማቶች በማሸጋገር በአከባቢው ሁለንተናዊ ለውጥን ማምጣት ይገባል ብለዋል አቶ ፍቅሬ።
በአከባቢው የተገኘው ሠላም ዘላቂ እንዲኾን ሁሉም የአከባቢው ነዋሪ የሠላም አምባሳደርነት ሚናውን መወጣት እንዳለበትም አቶ ፍቅሬ አስገንዝበዋል።
የተቋም ግንባታው የተጀመረውን ልማት በማስቀጠል የዜጎችን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ መሠረት እንደሚኾን የገለጹት ኃላፊው፥ በወረዳው ለሚገነባው የፓርቲ ህንጻ አባላትና ደጋፊዎች ቀጣይነት ያለውን ድጋፍ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
“የብልፅግና ፓርቲ ያልማል፣ ያቅዳል፣ ይፈጽማል” ያሉት አቶ ፍቅሬ የቢሮ ግንባታው በተቀመጠለት ደረጃ በቀጣይ ከአንድ ዓመት በነሰ ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለ ለአግልግሎት መብቃት እንዳለበት ተናግረዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ለትውልድ የሚሰራ ፓርቲ ነው ያሉት የምዕራብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታምሩ ቦኒ፥ ይህንንም ተግባር ለማከናወን የተቋም ግንባታ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መኾኑን ተናግረዋል።
የብልፅግና ፓርቲ በሁሉም መስክ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌትነት ሀገር ለማሻገር እየሰራ እንደኾነም አቶ ታምሩ የገለጹት።
በወረዳው ጀባ ከተማ የሚገነባው ባለሁለት ወለል የፓርቲ ህንጻ ከ86 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ እንደሚገነባም ነው ዋና አስተዳዳሪው የገለጹት።
በመርሐግብሩ ላይ የክልል፣ የምዕራብ ኦሞ ዞንና የጀባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች እና የአከባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
