





የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ፋይናንስ ቢሮ እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች 4ኛ ዙር የጋራ ምክክር መድረክ በሚዛን አማን ከተማ እየተካደ ይገኛል።
“የመንግሥት እና የሲማድ አጋርነትና ትብብር ለላቀ የህብረተሰብ ተጠቃሚነት”በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ የሚገኘው ምክክር መድረክ ላይ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ አቶ ተመስገን ከበደ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም የለወጡ መንግስት በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ወደ ክልሉ በመግባት የክልሉን የልማት ክፍተት በመለየት የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት እያረጋገጡ የሚገኙ የሲቪክ ማህበራት ቁጥር እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ተሳትፈው የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር የራሳቸውን አስተዋፅኮ እያበረከቱ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች በክልሉ ያለውን አስተማማኝ ሠላም እና ምቹ አጋጣሚዎችን ተጠቅመው በልማት ስራ እንዲሰማሩም አቶ ተመስገን ጥሪ አስተላልፈዋል።
የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንዳሉት፣የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን በጤና ዘርፍ ፤በአካባቢ ጥበቃ፤በትምህርት፤በውሃ ልማት፤ በሴቶችና ህጻናት መብቶች እንዲሁም በስርተ ምግብ ዘርፎች ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል።
በክልላችን ካለን የመልማት አቅምና ካለው የልማት ክፍተት አንጻር አሁንም በርካታ ስራ ይጠይቃል ያሉት በአከባቢው የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች መደገፍና የሚያጋጥማቸው ችግሮችን በመፍታት ረገድ በትኩረት እየተሰራ ነው መሆኑንም ተናግረዋል።
የክልሉን ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በተጨባጭ እንዲረጋገጥ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀራረብ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰው ወደ ክልሉ የሚመጡ ድርጅቶችን አቅምና ፍላጐት በመለየት እና አስፈላጊውን ድጋፍ በማደድረግ ህብረተሰቡን ፍትሀዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በክልሉ ያለው እምቅ አቅምን ወደ ተጨባጭ ሀብት ለመቀየርና የክልሉን ህዝብ መሠረታዊ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ እንዲቻል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጀቶችን ቁጥር መጨመር እንደሚገባ አሳስበዋል።
በአሁኑ ስዓት የውይይት መነሻ ሰነድ በክልሉ ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ዳይሬክተር በሆኑት ወ/ሮ አበራሽ አርጋው እየቀረበ ይገኛል።
በካሳሁን አሰፋ
