



የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ስራና ክህሎት ቢሮ ክልላዊ የክህሎት መር የስራ ዕድል ፈጠራ የንቅናቄ መድረክ ተጠናቋል።
በክህሎት መር የንቅናቄ መድረክ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በነበረው ውይይት ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ አስተያየቶችን ሰጥተዋል።
ተሳታፊዎች ባነሱት አስተያየት በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ብቁና ጥራት ያለው ሰልጣኝን ከማፍራት አንጻር ክፍተቶች መኖራቸውንና ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የስራ ስምሪት ላይ ስራአጥ ዜጎችን ከማሰማራት አኳያም ያለውን ጅምር ስራ አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል ።
በዚህ ዘርፍ ከቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጅ አጫጭር ስልጠናዎችን ቢወስዱም ፓስፖርት ለማውጣት ወጣቶች እየተቸገሩ መሆኑና ይህም ችግር እንዲቀረፍ ጠይቀዋል።
በአካባቢ ያሉ ጸጋዎችን መሠረት ያደረገ የስልጠና ፍላጎት እውን ማድረግ ብንጀምርም የስልጠና ቁሳቁስ ከማሟላት አንጻር ትኩረት እንዲሰጠውም ተጠይቋል።
ወጣቶችን በመካናይዜሽን የግብርና እርሻ ስራዎች ከማሰማራት አንጻር በየዞኑ መሠረታዊ ችግሮች ያሉበት መሆኑንና ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ተሳታፊዎች አንስተዋል።
ለወጣቶች የተሰራጨ ብድር አመላለስን በተመለከተም ችግሮች መኖራቸውንና ይህንንም በፍጥነት በማረም በቅንጅት ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ መድረኩን ባጠቃለሉበት ወቅት በክልሉ ያሉ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆችን ተልዕኮን ለማስፈጸም በሚችል መልኩ አደረጃጀቶችን በመፈተሽ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
በኮሌጆች ሰልጥነው የሚመረቁ ሰልጣኞችን ወደ ስራ ለማሰማራት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የኢንተርፕራይዝ ቢዝነስ ፕላን አዘጋጅተው የሚመረቁበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባልም ብለዋል።
የብድር እመላለስ እና ብድር ስርጭት የአሰራር ስርዓቱን ተከትሎ መከናወን እንዳለበትም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል ።
በክልሉ ትኩረት የተሰጠው የወጣቶች እርሻ ስራዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊሰራባቸው እንደሚገባም አሳስበዋል ።
የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ እንዳሻው በሰጡት ሀሳብ ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማጠናከር ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጆች የሚጠበቅባቸውን ውጤት ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ውጤታማ ኢንተርፕራይዞችን በሞዴልነት በመጠቀም ስራአጥ ወጣቶችን ወደ ስልጠና ማዕከል ማስገባት ይኖርብናል ብለዋል።
ለሁለት ተከታታይ ቀናት የነበረው የክህሎት መር የንቅናቄ መድረክ የተለያዩ አስተያየቶች እና ማብራሪያ የሚሹ ጉዳዮች ተነስው ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ተጠናቋል።
በታጠቅ አበበ
