




የመጋቢት 2010 ዓ.ም ለውጥ በሀገራችን ካስመዘገባቸው ስኬቶች መካከል በኃይል ዘርፍ ያመጣው እመርታ ተጠቃሽ ነው።
የመደመር መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣበት መጋቢት 2010 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ የኃይል አማራጮችን ከማስፋት አንስቶ ተጓትተው የነበሩ ሜጋ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ላይ ሰፊ ሥራዎችን አከናውኗል።
የመጀመሪያው ወሳኝ የማስተካከያ እርምጃ የተወሰደው በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ሲሆን፤ ግድቡን ከነበረበት ችግር ለማላቀቅ የተወሰደው እርምጃ የአፍሪካ ግዙፉ ፕሮጀክት ከፍጻሜ እንዲደርስ ያስቻለ ታሪካዊ ውሳኔ ነበር።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የሀገራችንን የኃይል አቅርቦት በእጥፍ ከማሳደግ ባሻገር የታዳሽ ኃይል ሽግግሯንም ያፋጠነ ነው።
የሕዳሴ ግድብ ከተጠናቀቀ በኋላ በሀገር ውስጥ ያለውን የኤሌክትሪክ ተደራሽነት መጠን ከማስፋት በተጨማሪ ለጎረቤት ሀገራት ንጹሕ ኢነርጂ በማቅረብ የገቢ ምንጭ ሆኗል።
በዚህ ያላበቃው የኃይል ዘርፉን የማልማት ሥራ ሌላኛውን የአፍሪካ ግዙፍ ኮይሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ወደ ማጠናቀቁ አድርሶታል።
የመጋቢት ለውጥ ኢትዮጵያ የቀጣናው ታዳሽ እና ተደራሽ ኃይል ማዕከል ለመሆን የሰነቀችውን ራዕይ በማዋለድ በተጨባጭ ለዓለም ማሳየት የቻለ ነው።
በውሃ ኃይል ያልተወሰነው ንጹሕ ኢነርጂ የማምረት እንቅስቃሴያችን ከንፋስ፣ ፀሐይ እና እንፋሎት ታዳሽ ኃይልን በማምረት ለቀጣናው ብሎም ለአፍሪካ ምሳሌ መሆን ችሏል።
ሀገራችን የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታን በይፋ የጀመረች ሲሆን፣ ይህንኑ ለማስፈፀም የኢትዮጵያ ኑክሌር ኃይል ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል።
በአጠቃላይ የመጋቢት 2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጥን ተከትሎ በኃይል ዘርፍ የተከናወነው ሥራ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ቀዳሚ የኃይል አምራች ሀገራት ተርታ አሰልፏታል።
ኢትዮጵያ በኃይል መሠረተ ልማት በፈጠረችው የተመቻቸ ሁኔታ በኢንዱስትሪ ፓርኮቿ እና በነፃ የንግድ ቀጣናዋ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን በማሳደግ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር ችላለች ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።
