
የክልሉ ደን አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ የክልሉን ኢኮኖሚ ዕድገት በላቀ ደረጃ ለማፋጠን ፣ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎችን በሀገር ደረጃ ከመጣው ለውጥ ጋር አስተሳስሮ የህዝብን መሰረታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችል ተግባራትን አስተሳስሮ ለመፈጸም በ2017 በጀት ዓመት አቅዶ ወደ ስራ ከገባ ወራትን አሰቆጥሯል ፡፡ ተቋሙ በደን ልማት፤ ጥበቃ እና አጠቃቀም ፤ በብዝሃ ህይወት ልማትና ጥበቃ፤ በአካባቢና አየር ንብረት ለዉጥ እና በአካባቢ እና ማህበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ ሲፈፅም ቆይቷል፡፡ በዚህም ተቋሙ ካቀዳቸው ግቦች መነሻነት እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ዙሪያ ከቢሮው ኃላፊ ጋር ቆይታ አድርገናል ፡፡ መልካም ንባብ !
በቅድሚያ ለቃለ ምልልሱ ፈቃደኛ ስለሆኑ አመሰግናለሁ። እኔም አመሰግናለሁ!
መኮ :_እንተዋወቅ ስምና ኃላፊነትዎን ቢገልጹልኝ ?
ዶ/ር. ኢ/ር. አስራት ገ/ማሪያም
የክልሉ ደን አካባቢ ጥበቃ እና ኤር ንብረት ለዉጥ ቢሮ ሃላፊ
መኮ:_ በክልሉ ባለፉት ወራት የአካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ስራዎች አተገባበር ምን ይመስላል ?
ዶክተር አስራት ገ/ማሪያም
ባለፉት ወራት ቢሮዉ ከተቋቋመለት ዓላማ አንፃር በርካታ ተግባራትን ስያከናዉን የቆዬ ሲሆን በክልሉ ዉስጥ ባሉ መዋቅሮች አፈፃፀሙ የተለያየ ቢሆንም በጥቅሉ ክልላዊ አፈፃፀሙ የተሻለ ነበር፡፡
መኮ:_ ተቋሙ በምን በምን ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ ተግባራትን ሲፈጽም ቆይቷል?
ዶ/ር. ኢ/ር. አስራት ገ/ማሪያም
ተቋሙ በደን ልማት፤ ጥበቃ እና አጠቃቀም ፤ በብዝሃ ህይወት ልማትና ጥበቃ፤ በአካባቢና አየር ንብረት ለዉጥ እና በአካባቢ እና ማህበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ ሲፈፅም ቆይቷል፡፡
መኮ:_ ተቋሙ ከሚያከናወናቸው ተግባራት በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ እስካሁን ያለው አፈጻጸምን ቢጠቅሱልኝ?
ዶ/ር. ኢ/ር. አስራት ገ/ማሪያም
የአረንጓዴ አሻራ ስራ ለተቋሙ መደበኛ ስራዉ ሲሆን መንግስት ለዘርፉ በሰጠዉ ልዩ ትኩረት እና መልካም ዕድል በመጠቀም ሌሎች ሴክተሮችን በማስተባበር ተግባሩን በተቀናጄ ሁኔታ እንፈፅማለን፡፡ በዚሁም መሰረት በክረምቱ መርሃ ግብር ብቻ 32.8 ሚልዮን ችግኝ በመትከል 10.933 ሄክታር መሬት ለመሸፈን ታቅዶ 41.43 ሚሊዮን ችግኝ የተተከለ ሲሆን በዚሁም 13810 ሄክታር መሬት መሸፈን ተችሏል፡፡ በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ 15.5 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ 20.52 ሚሊዮን ችግኝ መትከልም ተችሏል፡፡
መ/ኮ፡-ለዘንድሮ ተከላ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ያሉበትን ደረጃ ሊጠቅሱልኝ ይችላሉ?
ዶ/ር. ኢ/ር. አስራት ገ/ማሪያም
በዘንድሮ ዓመት 123.3 ሚሊዮን ችግኝ በማዘጋጀት እስከ መስከረም 2018 ዓ/ም ድረስ 98.64 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል የታቀደ ሲሆን በአንድ ጀንበር ተከላ 14.51 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዷል፡፡
መኮ:_ እስካሁን በተተከሉ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ክልላዊ የደን ሽፋኑን በምን ያህል ማሳደግ ተችሏል?
ዶ/ር. ኢ/ር. አስራት ገ/ማሪያም
አሁን ባለዉ ሁኔታ የክልሉ የደን ሽፋን 42.99 በመቶ ደርሷል፡፡
መኮ:_ ክልሉ ባሉት ጥብቅ ደን/ ባዮስፌር/ ህብረተሰቡ ደንን ጠብቆና ተንከባክቦ ላቆየው ከካርቦን ልቀት ተጠቃሚ እንዲሆን እየተደረገ ያለው ጥረት እንዴት ይገለጻል ?
ዶ/ር. ኢ/ር. አስራት ገ/ማሪያም
የክልሉ ህዝብ ከተፈጥሮ ሃብት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም ዉስጥ ጥቂቱን ለመጥቀስ ያህል፡
- የካፋ እና ሸካ ባዮስፌሮችን አሁናዊ ይዘት በማጥናት ለዮኔስኮ በማቅረብ የፈቃድ ዕድሳት ስራ ተጀምሯል፡፡
- ከተለያዩ የፌዴራል ተቋማት ጋር በመተባበር የክልሉን ተፈጥሮ ሃብት የአማቂ ጋሶች የመምጠጥ አቅም የማጥናት ስራ ተጀምሯል፡፡
- ለካርቦን ክፍያ ስርዓት አስፈላጊ መረጃ መሰብሰብ የሚያስችል ላቦራቶሪ በክልሉ ዉስጥ ለማቋቋም በሬድ ፕላስ እና በፋኦ ትብብር አስፈላጊ ግብዓቶች ግዥ የተፈፀመ መሆኑ እና ሌሎችም በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸዉ፡፡
መ/ኮ ፡- ሰሞኑን ደረቅ የአየር ንብረትን ተከትሎ የእሳት ቃጠሎዎች በየአካባቢው እየተስተዋሉ ነው ፡፡ የእሳት አደጋው በደን ላይ ያደረሰው ጉዳት ካለ ቢጠቅሱ ?
ዶ/ር. ኢ/ር. አስራት ገ/ማሪያም
በአሁኑ ወቅት ደረቅ እና ነፋሻማ የአየር ንብረትን ተከትሎ በክልላችን ካሉ መዋቅሮች ከሽካ ዞን በስተቀር በ5ቱ ዞኖች ስፋትና የጉዳቱ መጠን የተለያየ የደን እሳት ቃጠሎ ተከስቷል። እነዚህም፡-
1ኛ- ካፋ ዞን (አዲዮ ወረዳ፣በጠሎና በአዲዮ ድንበር ባለ ደን ላይ፣ ግምቦ ወረዳ ዳኪቲ ቀበሌ ጎባ ወረዳ እና ጋዋታ ወረዳ) ፡
2ኛ.ዳውሮ ዞን ( ማረቃ አደአ፣ ታርጫ ዙሪያ ወረዳ ፣ጌና፣ ዛባ ጋዞ፣ ማሪ ማንሳ፤ካጪ
እና ሎማ ወረዳ)
3ኛ-ም/ኦሞ ዞን (ሱርማ፣ ጋቺትና ሜ/ሻሻ)
4ኛ- ቤ/ሸኮ ዞን (ሸኮ፤ ጉራፋርዳ፤ ሰ/ቤንች እና ደ/ቤንች)
5ኛ- ኮንታ ዞን (ጰራ አንቻኖ፤ጪዳ ከተማ አስ/ር እና አማያ ዙሪያ)
ቃጠሎዉ በሰዉ አካል ላይ፤ በተፈጥሮ ሃብት፤ በሰብል እና ሌሎች ንብረቶች ላይ ጉዳት አድርሷል፡
የቃጠሎው መነሻ ህገ ወጥ ከሰል ምርት፡ የንብ ቀፎ ለማዉረድ የሚቀጣጠል እሳት እና ጥንቃቄ የጎደለው ቆሻሻ እና ተረፈ ምርት ማቃጠል መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል።
መ/ኮ ፡- ህብረተሰቡ ደንን ጠብቆ የማቆየት ልምዱ እጅግ የሚደነቅ ነው ይህንን ባህል ዘላቂ እንዲያደርገው የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ ቢገልጹልን ?
ዶ/ር. ኢ/ር. አስራት ገ/ማሪያም
የአካባቢው ማህበረሰብ የተፈጥሮ ሃብቱን በመጠበቅ እና በመንከባከብ ለትዉልድ ለማስተላለፍ ያበረከተዉ አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛ ስሆን ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ የመኖር ባህሉም ለዓለም ምሳሌ የሆነ ነዉ፡፡ በመሆኑም ይህ ባህል ከትዉልድ ትዉልድ እንዲተላለፍ በትኩረት መሰራት ያለበት ስሆን አሁን ያለንበት ወቅትም ለተፈጥሮ ሃብት ትልቅ ትኩረት የተሰጠበትና ከዘርፉም የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚረጋገጥበት ነዉ፡፡ በመሆኑም ይህንን አኩሪ ባህል በማጠናከር የተፈጥሮ ሃብቱ በዕዉቀት ተመርቶ አስፈላጊዉ ጥቅም ማግኘት እንዲቻል የማህበረሰባችንን ንቃተ ህሊና የበለጠ ማዳበር እና ባህሉንም ማጎልበት ተገቢ ነዉ፡፡
መኮ:_ የባለድርሻ አካላት ተሳትፏቸው እንዴት ይገለጻል ?
ዶ/ር. ኢ/ር. አስራት ገ/ማሪያም
የክልላችን መንግስት እና ገዢዉ ፓርቲ ለክልሉ ተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ የሰጡት ትኩረትና እየተደረገ ያለዉ ድጋፍ ከፍተኛ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸዉን ድጋፍ እያደረጉ ይገኛል፡፡
መኮ:_ ቀረ የሚሉትና ተጨማሪ ሀሳቦች ካሉ ቢያክሉበት?
ዶ/ር. ኢ/ር. አስራት ገ/ማሪያም
በየደረጃዉ ያሉ መዋቅሮች እና እያንዳንዱ ዜጋ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ጉዳይ የሚመለከተዉ መሆኑን በመገንዘብ ጉዳት ከመከሰቱ በፊት የመከላከል ስራ መስራት እንዲቻል እና አደጋ የሚያስከትሉ ምልክቶች ስታዩም ለሚመለከተዉ አካል በፍጥነት በማሳወቅ የድርሻዉን እንዲወጣ እንጠይቃለን፡፡
መኮ:_ለሰጡኝ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ ።
ዶ/ር. ኢ/ር. አስራት ገ/ማሪያም
አመሰግናለሁ፡፡
