ሪፖርታዥ”

Spread the love

በክልሉ የአርብቶ አደሩን ኑሮ መሠረት ያደረጉ ሁሉ አቀፍ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው፡- የክልሉ አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢ ጉዳይ ቢሮ

የክልሉን አርብቶ አደር አካባቢ እምቅ አቅም መሠረት ያደረጉና የህብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ነው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ታምሩ ቦኒ ገልፀዋል፡፡

በክልሉ በቆላማው አካባቢ አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር ማህበረሰብ ክፍሎች እንደሚኖሩ የተናገሩት አቶ ታምሩ የህብረተሰቡ የኑሮ ሁኔታ ተሻሽሎ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

በዚህም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ማስወገድና በግጭት መከላከል ዙሪያ ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ በመፍጠር ከ20 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት መደረጉን ያነሱት ኃላፊው እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ንቅናቄውን የማውረድ ስራ መከናወኑን ገልፀዋል፡፡

በክልሉ ውስጥ በሚገኙ አርብቶ አደር አካባቢዎች ግጭት ቀስቃሽ ሊሆኑ የሚችሉ 65 ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መለየታቸውንና እነዚህን የተለያዩ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመግታት ያለመ ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመፍጠር የጋራ አቅጣጫ በማስቀመጥ እየተሰራው መሆኑን አቶ ታምሩ ጨምረው አብራርተዋል፡፡

ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ላይ ለማህረሰቡ በተሰጠው ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በሠላምና ፀጥታው አሁን ላይ ተጨባጭ ለውጦች እየተመዘገቡ ማምጣታቸውን የጠቆሙት አቶ ታምሩ ቢሮው በቆላማ አካባቢ በሚኖሩ በከፊል አርብቶ አደር ማህበረሰብ ኑሮ ማሻሻያ ዙሪያም ላይ ትኩረት አድርጎ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የሆስቴል አገልግሎትን በተመለከተ በክልሉ ሁለት ሆስቴሎች አሉ ያሉት አቶ ታምሩ ባሉን ሁለቱ የሚዛን አማንና በሱሪ ወረዳ የኪብሽ ሆስቴሎች 179 ተማሪዎችን በመቀበል አስፈላጊው የትምህርት ግብአት ተሟልቶላቸው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ አንስተዋል፡፡

ቢሮው ባመቻቸው መንገድ በትምህርትና ስልጠና በመጀመሪያ ድግር 116 ተማሪዎች እና በድፕሎማ 42 በአጠቃላይ 158 ተማሪዎችን በተለያዩ ሙያ ዘርፎች በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ እና በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

በክልሉ የአርብቶ አደሩን ኑሮ መሠረት አድርገው የተቀረፁ ሶስት ፕሮጀክቶችን መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ታምሩ ፕሮጀክቶቹ በዋናነት በምዕራብ ኦሞ ዞን 4 ወረዳዎችንና እና በካፋ ዞን 1 ወረዳን በማቀፍ በአጠቃላይ 5 ወረዳዎችን የመደገፍ ስራን እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በአርብቶአደሩ ማህበረሰብ አካባቢ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲሰሩ እንደ ቢሮው ብርቱ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ባለፉት 6 ወራት አፈፃፀሙ በተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን የገለፁት አቶ ታምሩ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑ ፕሮጀክቶችን ህብረተሰቡ በተገቢው በመንከባከብ እና በመጠበቅ መጠቀም እንደሚገባው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ከመሠረተ ልማት አንፃር በ2017 የበጀት ዓመት በግማሽ ዓመቱ በርካታ የተጠናቀቁና የህዝብን ችግር ልቀርፉ የሚችሉ በመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት፣ የመንገድ፣ የድልድይ እና የትምህርት ቤት ግንባታ ፕሮጀክቶች 89 ሚሊዮን 216 ሺህ 394.82 ብር የገንዘብ ወጪ ተጠናቀው 68 ሺህ 300 የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል ኃላፊው፡፡

በቀሪዎቹ ወራት 81 ኪሎ ሜትር የመንገድ መሠረተ ልማት ስራ ለመጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን አንስተው የመንገዶች ስራ በሱሪ ወረዳ ከቱልጊት እስከ ከርሞጋ 20 ኪ.ሜ፣ በሜኤኒት ጎልዲያ ወረዳ ከጨበራ እስከ ያርጣ 30 ኪ.ሜ እና በካፋ ዞን ከኡፊት እስከ ኦሞ ኩራዝ 31 ኪ.ሜትር መንገድ መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡

የቢሮው ኃላፊው አክለውም ከፊል አርብቶ አደር ማህበረሰብ አካባቢ በኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራሞች ላይ ትኩረት በማድረግ ፍራፍሬንና ስራስር ሰብሎችን በማምረት የምግብ ዋስትናን አረጋግጠው ለሌሎችም ሞዴል የሚሆኑበት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

አርብቶ አደሩ ካለበት ከልማት እና ከመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲወጣ የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት አቶ ታምሩ በየጊዜው ተጠናቀው ለማህበረሰቡ አገልግሎት ክፍት የተደረጉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች የማስተዳደር ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *