በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚያስችል አቅም እንዳለ በተግባር ማረጋገጥ ተችሏል – ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር)

Spread the love

በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚያስችል አቅም እንዳለ በተግባር በማረጋገጥ ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር) ገለጹ።

“ሉዓላዊነት በምርታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የፓናል ውይይት በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የምግብ ሉዓላዊነት የኢትዮጵያ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) መድረኩን በከፈቱበት ወቅት ገለጸዋል።

ባለፉት ዓመታት ይህንን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን ጠቅሰው፤የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል አቅም እንዳለም ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።

በቤተሰብ እና በግለሰብ ደረጃ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራዊ ለውጦች መመዝገባቸውንም አንስተዋል።

ለፍጆታ የሚውሉ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ከውጭ የማስገባት ልምምድን መቀነስ መቻሉን ጠቅሰው ትርፍ በማምረት ከራስ አልፎ ለሌሎች ማቅረብ እንደሚቻልም በተግባር ማየት መቻሉን ተናግረዋል።

በመሆኑም ይህንን አጠናክሮ ለመቀጠል በቅንጅትና በጋራ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው መሰል መድረኮች የላቀ ጠቀሜታ እንዳላቸው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በመድረኩ የምግብ ሉዓላዊነት ከሀገር ሉዓላዊነት ጋር ያለው ትስስር፣ከብሔራዊ አደጋ ስጋት ቅነሳ ፖሊሲ አኳያ ያለው መስተጋብር እንዲሁም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሚና የተመለከቱ መነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።

በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ያሉ ምቹ ሁኔታዎች በውይይቱ በስፋት እንደሚዳሰሱም ይጠበቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *