




በ2016 የበልግ አዝመራ ወቅት በክልሉ ከ354 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል ፡፡
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በመገባቱ የተሻለ አፈጻጸም እየታየ ነው ፡፡
ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የአፈር ማዳበሪያና የምርጥ ዘር አቅርቦት መሻሻሎች እንዳሉት ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮች ተናግረዋል ፡፡
በቤንች ሸኮ ዞን በሰብል አብቃይነቱ ከሚታወቁት ወረዳዎች አንዱ የደቡብ ቤንች ወረዳ ሲሆን በዘንድሮ በልግ እርሻ የተሻለ ምርት ለማግኘት በትኩረት መሰራቱን የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኪዳኔ ሺቅ ተናግረዋል ፡፡
በወረዳው በበልግ በዋና ዋና ሰብል ከለማው 4 ሺህ 7 መቶ ሄክታር መሬት ውስጥ 3 ሺህ 7 መቶ ሄክታር የተሟላ የግብርና ግብኣቶችን በመጠቀም እየለማ እንደሚገኝና ከዚህም ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚሸፍነው የበቆሎ ሰብል መሆኑንም አቶ ኪዳኔ ሺቅ ተናግረዋል ፡፡ በወረዳው 150 ክላስተር የበቆሎ ሰብል እየለማ ሲሆን ከዚህም ውስጥ በዞዞ ቀበሌ የብርካሽ ክላስተር 150 ሄክታር በቆሎን በተሟላ የግብርና ግብኣት የለማ ነው ብለዋል ፡፡
አርሶ አደር ዶርጭ ተረባና አርሶ አደር ስንታየሁ ባይኩ በዞዞ ቀበሌ የሚኖሩ አርሶ አደሮች ሲሆኑ በዘንድሮው በልግ የግብኣት አቅርቦቱ የተሻለ በመሆኑ ወቅቱን ጠብቀን በመዝራታችን የተሸለ ምርት እናገኛለን ሲሉ ተናግረዋል ፡፡
በካፋ ዞን ጊንቦ ወረዳ የሾምባ ሼካ ቀበሌ የሰብል ልማት ባለሙያ የሆኑት አቶ መስፍን መንገሻ በሰጡት ማብራሪያ 547 ሄክታር መሬት በበቆሎ ሰብል ለመሸፈን አቅደው 399 ሄክታር መሬት በበቆሎ ሰብል የተሟላ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ማልማት መቻሉንና በጎጀብ ክላስተር 38 ሄክታር መሬት በበቆሎ ሰብል መሸፈኑንም አስረድተዋል ፡፡
በቀበሌው ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አሸብር አሰፋው በዘንድሮ የበልግ እርሻ ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ወደ ስራ በመግባታቸውና ተገቢውን ግብርና ግብኣት በወቅቱ በማግኘታቸው የተሸለ ምርት ለማግኘት የሚያስችላቸውን ስራ መስራታቸውን ተናግረዋል ፡፡
ዘንድሮ የተደረገው ቅድመ ዝግጅት ስራ ከዚህ ቀደም ከነበረው በእጅጉ የተሻለና አሁን ላይ ያለው ቡቃያ የተሸለ ምርት እንደሚገኝበት ተስፋን የሰነቀ ነው ብለዋል አርሶ አደር አሸብር፡፡
የካፋ ዞን ግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጋዎ አባመጫ እንደተናገሩት በዞኑ በዘንድሮ በልግ እርሻ በዋናነ ሰብሎችና በሆልቲካልቸር ሰብሎች ከ86 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል ፡፡
በዞኑ የቀረቡ የግብርና ግብኣቶችንም በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ የሻለ ምር ለማግኘት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም አቶ ጋዎ አስረድተዋል ፡፡
የቤንች ሸኮ ዞን ግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ልማት መምሪ የእርሻና ህብረት ስራ ልማት ዘርፍ ኃላፊና ምክትል መምሪያ ኃላፊ አቶ መኳንንት ሀይሉ በሰጡት ገለጻ በዞኑ በዋና ዋና ሰብሎችና በሆልቲካልቸር ሰብሎች ከ94 ሺህ በላይ ሄክታር በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል ፡፡
በዋና ዋና ሰብሎች 64 ሺህ 379 ሄክታር ከለማው ውስጥ 25 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ ማሳ የተሟላ የግብርና ግብኣቶችን በመጠቀም እንደለማ አስረድተዋል ፡፡በዞኑ የሚታየውን የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ በአርሶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከላት 68 ሄክታር የተለያዩ ዝርያ ያላቸውን የምርጥ ዘር ብዜት ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙም አብራርተዋል ፡፡
በክልሉ ግብርና ቢሮ የግብርና ግብዓትና ገጠር ፋይናንስ ዘርፍ ኃላፊና ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አስራት አሰፋ በመኸር፣በመስኖና በበልግ የእርሻ ወቅት 194 ሺህ 600 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ እስካሁን ከ183 ሺህ በላይ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ቀርቦ ከ100 ሺህ ኩንታል በላይ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ተናግረዋል ፡፡
በክልሉ ግብርና ቢሮ የእርሻ ዘርፍ ኃላፊና ምክትል ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ አሸናፊ ክንፉ በዘንድሮ በልግ እርሻ ከ354 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በዋና ዋና ሰብሎችና በሆርቲካልቸር ሰብሎች በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል፡፡
በበልግ አዝመራ በክልሉ የተሻለ የግብርና ግብኣት አቅርቦት በወቅቱ መቅረቡ የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖር ያስቻለ ሲሆን የአርሶ አደሩ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከአምናው በተሻለ መልኩ መሻሻል አሳይቷል ብለዋል ፡፡
በታጠቅ አበበ
