በክልሉ የተገኘውን ሠላም ለማጽናት የምክር ቤቱ አባላት የሠላም አምባሳደርነትን ሚና መጫወት እንዳለባቸው ተመላከተ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የበሔረሰቦች ምክርቤት በአሰራርና አባላት ሥነምግባር ድንብ እና ዘላቂ ሠላም ግንባታ ዙሪያ ለምክር ቤት አባላት በቴፒ ከተማ ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ የተሳተፉ የባለድርሻ አካላት በክልሉ የተገኘውን አንጻራዊ ሠላም ለማጽናት የምክር ቤቱ አባላት የሠላም አምባሳደርነትን ሚና መጫወት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

በክልሉ ከጥቂት አመታት በፊት ይስተዋል የነበረውን የሠላም መደፍረስ በንግግርና ወይይት በመፍታት ችግር ዉስጥ የነበሩ አከባቢዎችን ለኑሮ፣ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ምቹ መደላድል መፈጠር መቻሉን የገለጹት የመድረኩ ተሳታፊዎች ይህንን ሠላም ለማጽናት የህዝብ ለህዝብ ግኑኝነት ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

በክልሉ ህዝቦች መካከል በመከባበርና መቻቻል መርህ የቆየውን የህዝቦችን አንድነት በማጠናከር ዘላቂ ሠላምና ልማት ማረጋገጥ፣ የሚከሰቱ ችግሮችን በአብሮነት በመፍታት ለሌሎች ተምሳሌት መሆን እንደሚገባም ነው ተሳታፊዎቹ የገለጹት።

“ስልጠናው እንደ አባል መብትና ግዴታዎችን በመለየት በየአካባቢው ለግጭት መነሻ የሚሆኑ ጉዳዮችን ለይተው በአብሮነት ዕሴት መርህ ላይ ተመርኩዞ ለመፍታት አቅም ፈጥሯል” ያሉት ተሳታፊዎቹ በክልሉ አንዳንድ አከባቢዎች ከልማትና መልካም አስተዳደር ጋር የሚነሱ በተላይም በአርብቶአደር አከባቢ የፍትሐዊነት ጥያቄዎች ትኩረት የሚሹ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በየደረጃው ያሉ የምክር ቤት አባላት በሠላም ዕሴት ግንባታ ላይ በግንባር ቀደምትነት በመሳተፍ በክልሉ ዘላቂና አስተማማኝ ሠላም በማስፈን ልማትና ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚገባ የተጠቆመ ሲሆን አስተሳሳሪ ትርክቶች በማጎልበት፣ክልላዊ አብሮነት በማጠናከር የአንድ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ መገንባት እንደሚገባም ነው የተገለጸው።

ተሳታፊዎቹ አክለው ስልጠናው የወከለውን ህዝብ በታማኝነት፣በግልጽነት እና በቅንነት ለመስራት ተጨማሪ አቅም የፈጠረ እንደሆነና ቀጣይ እንዴ አንድ አባል ሚናውን ለይተው ለህዝብ ጥቅም ለመወገን የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል።

ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽና ማጠቃለያ የሰጡት የምክር ቤት ዋና አፌ ጉባኤ የተከበሩ አቶ መቱ አኩ በጉልህ ለሚነሳው የበጀት ቀመር ጥያቄ ግልጽና አሳታፊ ለማድረግ ጥረት መጀመሩን አንስተዋል።

በሠላም ዕሴት ግንባታ ላይ የምክር ቤቱ አባላት ቁርጠኝነት መጠናከር እንዳለበት ያሳሰቡት ዋና አፌ ጉባኤው ከምክር ቤቱ የውስጥ አሰራር ጋር የተነሱ የግልጽነት ጥያቄዎችን በቀጣይ ከሌሎች አቻ ምክር ቤቶች ጋር በመናበብ ለመፍታት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ የሚነሱ የህዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት ከሌሎች ባለድርሻ አካላትና ከተቋማት ጋር ተቀናጅተው እየሰራ እንደሚገኝ ያብራሩት የምክር ቤቱ ምክትል አፌ ጉባኤ የተከበሩ አቶ መለሰ ከበደ በሁሉም ዘርፍ ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመረውን እንቅስቃሴ ከግብ እንዲደርስ የምክር ቤቱ አባላት ቁርጠኝነት መጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *