







በቴፒ ከተማ ስካሄድ የነበረው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ብሔረሰቦች ምክርቤት 2ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ጉባኤ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ ተግባራት አፈጻጸም በመገምገምና በቀጣይ የትኩረት መስኮች ላይ በመምከር ተጠናቋል።
በጉባኤው የዘጠኝ ወራት ዝርዝር የተግባር አፈጻጸም በምክር ቤቱ ምክትል አፌ ጉባኤ የተከበሩ አቶ መለሰ ከበደ ቀርቧል።
በዚህም ምክር ቤቱ በህገመንግስቱ በተሰጠው ስልጣን መሠረት በጋራ ዕሴት ግንቦት፣ ህገመንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ እንዲሁም በሌሎችም ተልዕኮዎች የተሻለ ተግባር ማከናወኑ ተብራርቷል።
በቀረበው ሪፖርት መነሻ ከምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ጥያቄና አስተያየቶች የተሰጡት ሲሆን በተለይም ዜጎችን በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማስቻል የተጀመረው የግንዛቤ ፈጠራ ስራ እጅግ የሚበረታታ በመሆኑ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በትኩረት መሰራት እንዳለበት ተጠይቋል።
ክልሉ ከሌሎች ክልሎች ጋር ወሰን በሚጋራባቸው ቀጠናዎች እንዲሁ በአርብቶአደር አካቢ አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ ለግጭት መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ችግሮችን በወንድማማችነት መርህ ላይ በመቆም በንግግር በውይይት መፍታት እንደሚገባ ያሳሰቡት የምክር ቤቱ አባላት ሠላምን ለማጽናት ህብረተሰቡን አሳትፎ መስራት ይገባልም ብለዋል።
በሁሉም ዘርፍ ፍትሃዊነትን ለማስፈን ችግሮችን በጥናት በመለየት ጉድለት መሙላት ይገባል ያሉት ተሳታፊዎች በአርብቶአደር አከባቢ ከመሠረተ ልማት አለመሟላት ጋር ተያይዞ ለግጭቶች አባባሽ የኾኑ ጉዳዮች ተገቢው ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል።
ህብረተሰቡ ለራሱ ሠላም ዘብ እንዲቆም ማድረግ ወጣቶችንና ሴቶች በሠላም ጉዳይ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ በክልሉ በ7 ቋንቋዎች በሬዲዮ የተጀመረው የሠላም ዕሴት ግንባታ የሚዲያ ስራ በተቀሩት 6 ቋንቋዎች መሰጠት እንዳለበት ተነስቷል።
ተግባራትን በተፈለገው ጊዜ ሁኔታ ለማሳካት የበጀት ውስንነትና የሰው ሀይል አለመሟላት አንዱ ማነቆ መኾኑ አሳሳቢ በመሆኑ ቀጣይ የክልሉ የአስፈጻሚው አካላ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት መደገፍ እንዳለበትም ነው አባላቱ ያነሱት።
የምክር ቤቱን አሰራር የሚደግፉ ሀሳቦች ከአስፈፃሚው የመንግሥት አካላት የተሰጡ ሲሆን የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ በክልሉ ከልማት ወደኋላ የቀሩትን አካባቢዎች በቀጣይ የእቅድ አካል በማድረግ ለመደገፍ በጋራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
አቶ ፀጋዬ አክለው በቀደመው ክልል የነበሩ የጋራ ቋሚ ሀብቶችን የፌዴራል መንግሥት በሰጠው አቅጣጫ መሠረት ኮሚቴ ተዋቅሮ የክፍፍል ስራው በፍትሀዊነት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ አንዳንድ አከባቢዎች የሚነሱ የእርስበርስ ግጭትና አለመግባባቶችን መንግሥትና መሪው ፓርቲ ለመፍታት በሚያደርገው ጥረት የአከባቢው ተወላጆችና አመራሮች ድጋፍ መጠናከር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸው የተነሱት የልማት የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን የክልሉ መንግሥት አቅም በፈቀደው እንደሚያከናውን በመግለጽ በክልሉ ህዝቦች መካከል ያለው ትብብርና አንድነት መንፈስ መጠናከር አለበት ብለዋል።
ምክር ቤቱ የጋራ ዕሴቶችን በማጎልበት ክልላዊ አንድነትን ማጠናከር የጀመረው የጋራ ዕሴት ጥናት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አቶ ማስረሻ ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የምክር ቤቱ ዋና አፌ ጉባኤ የተከበሩ አቶ መኩ አኩ በበጀት ዓመቱ በጠንካራ የተነሱ ጉዳዮችን በማስቀጠል ቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ዋና አፌ ጉባኤው አካለው ተግባራትን ለማሳለጥ ከአስፈፃሚው አካላት የተጀመረው ቅንጅት የማጠናከር እንዲሁም ከሌሎች ከአጎራባች ክልሎችም ጋርም በትብብር መንፈስ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በመጨረሻም ምክር ቤቱ በምክር ቤቱ መቋቋሚያ አዋጅ መሠረት እያንዳንዱ 7 አባላት ያሉትን የህግ ጉዳዮች እና የበጀት ጉዳዮ ቋሚ ኮሚቴዎች አደራጅቷል።
በዕድገቱ በዛብህ
