




የህዝቦችን ተጠቃሚነትና የተመጣጠነ እድገት ለማረጋገጥ ገቢ የማመንጨት አቅምን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያዘጋጀው የጋራ ገቢዎች አስተዳደርና ክፍፍልን በተመለከተ የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ አካላት የጋራ ምክክር መድረክ በሀዋሳ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር እንደገለጹት፤ የሀገሪቱ የጋራ ገቢዎች ቀመር ከ20 ዓመት በላይ ሲያገለግል ቆይቷል።
ቀመሩ ከ2013 በጀት ዓመት ጀምሮ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ማሻሻያ ተደርጎበት መተግበር ከጀመረ ወዲህ የክልሎች ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም የገቢ አቅምን በማጎልበት የሀገሪቱን ዜጎች እኩል ተጠቃሚነትና የተመጣጠነ እድገት ለማረጋገጥ ገቢ የማመንጨት አቅምን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም የሚሰበሰበው የጋራ ገቢ አስተዳደርና ማስተላለፍ ሥርዓት የበለጠ ግልጽነት የተላበሰ፣ ቀልጣፋና ተጠያቂነትን ያረጋገጠ እንዲሆን ያስፈልጋል ብለዋል።
በዚህ ዙሪያ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቅረፍም የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ አካላት ጠንካራና ቀጣይነት ያለው ቅንጅት ሊፈጥሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የመድረኩ ዋና ዓላማም አዲሱ የጋራ ገቢዎች ቀመር ተሻሽሎ ስራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ በምክር ቤቱ ውሳኔ መሠረት እየተተገበረ መሆኑን ለመገምገም መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም ክልሎች በተዘረጋው ሥርዓት ላይ ያላቸውን እምነት ለማጎልበት፣በክዋኔ ኦዲት ውጤት መሠረት ጠንካራ ጎኖችን አስቀጥሎ ያሉትን ችግሮች በማስወገድ ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ታስቦ መሆኑን አብራርተዋል።
በተለይ ከጋራ ገቢዎች አንዱ የሆነው የማዕድን ገቢ አሰባሰብና አስተዳደር ረገድ ያለውን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም በኩል ቀጣይ ሥራ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
በምክር ቤቱ የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ፀሀፊ አቶ ሀይሉ ኢፋ በበኩላቸው፤ በተሻሻለው ቀመር መሰረት የክልሎች ድርሻ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንና መሠረታዊ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል።
ቀመሩ ከተሻሻለ በኋላ ለክልሎች ይከፋፈል የነበረው የድጎማ በጀት ማደጉንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በመድረኩ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች እንዲሁም የፌዴራል እና የክልል ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።
