በከተማው ዘላቂ የንጹህ ውሃ ማግኘት በመቻላቸው መደሰታቸውን ነዋሪዎች ገለጹ።

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፣ በምዕራብ ኦሞ ዞን በማጅ ቱም ከተማ አስተዳደር በባስኬት ፈንዴ ፕሮግራም፤ በውሃና ኢነርጂ ሚንስቴር በውሃ ልማት ፈንዴ በኩል በተገኘ 55 ከመቶ ብድር እና 45 በመቶ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር የወጪ መጋራት ድርሻ የተገነባው የቱም የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አግልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

ያነጋገርናቸው የቱም ከተማ ነዋሪዎች፥በከተማው ዘላቂ የንጹህ ውሃ ማግኘት በመቻላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ጤንነቱ ያልተጠበቀ ውሃ በመጠጣት ራሳቸውና የቤተሰብ አባሎቻቸው በተለያዩ ውሃ ወለድ በሽታ ይጠቁ እንደነበረ ያስታወሱት አስተያየት ሰጪዎቹ አሁን በከተማው ዘላቂና አስተማማኝ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ እየቀረበላቸው እንደሆነም ነው የገለጹት።

የማጅ ቱም ከተማ አስተዳደር ውሃና ፈሳሽ አግልግሎት ድርጅት ስራ-አስኪያጅ ወ/ሮ ትቅደም አበበ በበኩላቸው ተገንብተው ለአግልግሎት የበቃው የቱም ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከ10ሺህ ለሚበልጡ የቱም ከተማና ዙሪያ ቀበሌዎች አስተማማኝ የንጹህ መጠጥ ውሃ እንደሚያቀርብ በመግልጽ ተጠቃሚ ህብረተሰቡ የውሃ መሠረተ-ልማት ከብልሽት እንዲጠብቅ አሳስበዋል።

በከተማው ከዚህ በፊት አስተማማኝ የንጹህ መጠጥ ውሃ ባለመኖሩ ህብረተሰቡ ወራጅ ውሃን በመጠጣት ለተለያዩ የጤና ችግር ይጋለጥ እንደነበረ ያስታወሱት ስራ አስኪያጁ አዲሱ ፕሮጀክት ይህንን ችግር በዘላቂነት የሚቀርፍ እንደሆነም ተናግረዋል።

በፕሮጀክቱ በተገነባው የሳንቴሽን ማዕከል ለተደራጁ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው የገለጹት ወ/ሮ ትቅደም የከተማው ውሃ ከከፍተኛ ቦታ በተፈጥሮ ግፊት የሚመጣ በመሆኑ የውሃ መሳቢያ መግፊያ ፓምፕ፣ የሀይል አቅርቦትን የማይፈልግ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የውሃ ምንጭ (አይን) ያለበት አከባቢን ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ በማድረግ የምንጭ ዘላቂነቱን ማረጋገጥ እንደሚገባ ያሳሰቡት ስራ-አስኪያጇ በከተማው በተሻሻለው የውሃ ታሪፍ ገቢን በተገቢው በመሰብሰብ በሚገኘው ሀብት ለቦኖ መሠረተ ልማት ጥገናና የማስፋፊያ ስራዎች እንደሚውል ተናግረዋል።

በከተማው ተገንብተው ለአግልግሎት የበቃው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የ4 ምንጭ ግንባታና መልሶ ጥገና፣ የ 9.13 ኪ/ሜትር ዋና የግፊት መስመር ዝርጋታ ስራ፣ የ21.745 ኪ/ ሜትር ርዝመት የውሃ ማሰራጫ መስመር ዝርጋታ፣ 4 የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከር ግንባታ፣6 ቦኖዎች፣ የውሃ አገልግሎት ህንጻ ፣ ሞዳሌ የህዝብ መጸዳጃ ቤት ያካተተ መሆኑንም ነው ወ/ሮ ትቅደም የገለጹት።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *