



በክልሉ ብዙኅ ዋና ማዕከላት ከሚገነቡ የክልል ተቋማት ሕንጻዎች አንዱ የሆነው በታርጫ ከተማ የመሠረተ ድንጋይ ተቀምጧል።
የመሠረተ ድንጋዩን ያስቀመጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው ክልሉ ከተመሠረተ ወዲህ እየተከናወኑ የሚገኙ የሠላም፣ የልማትና መልካም አስተዳደር ሥራዎች የሕዝቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እያስነሱ የሚገኙትን ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶትን በማጠናቀቅና በማስመረቅ እንዲሁም አዳዲሶችንም የመገንባት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የሚገነባው ሕንጻ የተደራጀና የተጠናከረ የመረጃ አያያዝን በማጎልበት በአንድ ማዕከል ለተገልጋዮች የአገልግሎት አሰጣጡን ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ያስችለናልም ብለዋል።
የግንባታው ሂደት እንዳይስተጓጎል ክፊያዎቹ ሳይዘገዩ የሚከፈሉ ሲሆን በቀጣይም ልማቱ ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች የክልሉ መንግሥት በመንገድ።፣ በውኃና በተቋማት ግንባታ በትኩረት የሚሠራ እንደሚሆንም አስረድተዋል።
በዕለቱ የዳዉሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ እንደገለጹት የሕዝብ የዘመናት እኩል የመልማት ጥያቄ አሁን ላይ መልስ እያገኘ መምጣቱ ለሕዝቦች በአብሮነትና አንድነት ለመኖር ተስፋ ሰጪ እየሆነ ይገኛል።
ክልሉ ከተመሠረተ ወዲህ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እየተመለሱ ለመገኘታቸው ይህ ማሣያ መሆኑንም ገልጸዋል።
ስለሆነም በክልሉ ብዙኅ ዋና ማዕከል ታርጫ በክልል መንግሥት ወጪ ለሚገነባው ሕንጻ ዞኑ ከይገባኝ ነጻ የሆነውን ከ6 ሄክታር በላይ የሆነውን ይዞታ አዘጋጅቶ ማቅረቡንም አስረድተዋል።
የሕንጻው ግንባታ ለወጣቱ ተጨማሪ የሥራ ዕድል የሚፈጠርና ለከተማው ውበት እንደሚሆንም ገልጸዋል።
በመሠረተ ድንጋይ የማስቀመጥ መርሃ ግብር ላይ የክልሉ ርዕስ መስተዳድሩን ጨምሮ የክልሉ ዋና አፈ ጉባዔና የመንግሥት ዋና ተጠሪን እንዲሁም የክልሉ፣ የዞኑና የታርጫ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች፣ የሴቶችና ወጣቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።
አዲስ የሚገነባው ባለሰባት ወለል ሕንጻ ሲሆን በ2 ሺህ 600 ካሬ ላይ የሚያርፍ ይሆናል።
