ወጣቶች ሀገር ተረካቢ ብቻ ሳይሆኑ ሀገር በመገንባት ለትውልድ አሻጋሪ ትልቅ አቅሞች ናቸው ፦ አቶ ነጋ አበራ

Spread the love

“ከቃል እስከ ባህል ” በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ የውሳኔ አቅጣጫዎች ላይ የብልጽግና ወጣቶች ክንፍ ሚና በሚል መሪ ሀሳብ ከወጣቶች ጋር የውይይት መድረክ በሚዛን አማን ከተማ ተጀምሯል።

በዚሁ ክልላዊ የወጣቶች ክንፍ የንቅናቄ መድረክ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት በክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊና ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ ነጋ አበራ የብልጽግና ፓርቲ ከዕድሜው በላይ የሆኑ ትላልቅ ስኬቶችን ያስመዘገበ ፓርቲ መሆኑን ተናግረዋል ።

ፓርቲው ለዘመናት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሆነው የሰነበቱ የህብረተሰቡን የመልማት ጥያቄዎች የፈታ አዳዲስ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን እውን እያደረገ መምጣቱንም አቶ ነጋ አበራ አብራርተዋል ።

ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የተለመደው ነጠላ ትርክን የማስረጽ የፖለቲካ ባህልን በማስቀረት ብሔራዊነት ገዢ ትርክትን እውን በማድረግ የብልጽግና ፓርቲ ጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ እያከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል ።

በሁለተኛው መደበኛ የብልጽግና ፓርቲ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎችን ተከትሎ በሀገሪቱ የሰላምና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን ለማስረጽ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን አቶ ነጋ ገልጸዋል።

ይህንን ተከትሎም ከወጣቶች ጋር የሚደረገው ውይይትም የዚሁ አካል ጭምር መሆኑን አቶ ነጋ ገልጸዋል።

ወጣቶች ሀገር ተረካቢ ብቻ ሳይሆኑ ሀገር በመገንባት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ አስረካቢ መሆናቸውን ጭምር ገልጸዋል።

ወጣቶች በፓርቲው የተቀመጡ ውሳኔዎችን እና አቅጣጫዎችን የሚያሰርጹበት ብቻ ሳይሆን የወጣቶችን ጉዳይ የተመለከተ በቂ ግብዓት የሚሰበሰብበት መድረክ መሆኑንም ገልጸዋል።

ወጣቶች የፓርቲው ትልቅ አቅም በመሆናቸው ውሳኔዎችንና አቅጣጫዎችን በመፈጸምና በማስፈጸም ትልቅ ሚና እንዳላቸውም አቶ ነጋ በመድረኩ ገልጸዋል።

በልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ወጣቶች ቀጥተኛ ተጠቃሚ በመሆን የተያዙ ዕቅዶች እውን እንዲሆኑ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡም ጠይቀዋል ።

በብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ ስራ አስፈጻሚና የጽ/ቤቱ ምክትል ኃላፊ ወጣት ሰብለ በቀለ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጉዞ ውስጥ የብልጽግና ወጣቶች ክንፍ ወጣቶችን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ተግባራት ዘርፈ ብዙ ስራዎች መሰራታቸውን አንስተዋል።

የወጣቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ያለውን ስራና በቀጣይ በሚሰሩ ስራዎች ከቃል ወደ ባህል ለማሸጋገር የፓርቲውን ውሳኔዎችና የተቀመጡ አቅጣጫዎችን በትጋትና በቁርጠኝነት ለመፈጸምና ለማስፈጸም መድረኩ መዘጋጀቱን ወጣት ሰብለ ተናግረዋል ።

ወጣቶች ህብረብሔራዊነታችንን እንደ መልካም አጋጣሚ እና የእኛነት መገለጫ በማድረግ እኛነታችንን ይበልጥ አሰናስነን አብሮነታችንን ይበልጥ ማጠናከር ይጠበቅብናልም ብለዋል።

እንደ ሀገር በወጣቶች ክንፍ አደረጃጀቶች በተፈጠረው የውይይት መድረክ 5 ሚሊዮን ወጣቶች እንደሚሳተፉም ወጣት ሰብለ በቀለ ተናግረዋል ።

የቤንች ሸኮ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ደግፌ ኩድን ባስተላለፉት መልዕክትም የጋራ ገዢ የሆኑ ትርክቶችን በህብረተሰቡ ለማስረጽ ወጣቱ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የሀገር ፍቅርን በማጎልበት ብልጽግናን በማረጋገጥ የተገኘውን ውጤት ለማጽናት ወጣቶች በመደጋገፍ ካለፈው በበለጠ ሀገራዊ ድርሻቸውን ሊወጡ ይገባልም ብለዋል።

“ከቃል እስከ ባህል ” በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎች እና የተቀመጡ አቅጣጫዎች ላይ የብልጽግና ወጣቶች ክንፍ ሚና በሚል መሪ ሀሳብ በአቶ ወንዱ መንገሻ ሰነድ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ነው።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *