




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ፣ በገጠር ትስስር ለምግብ ዋስትና (RCFSP) ፕሮግራም አማካኝነት በ266.7 ሚሊዮን ብር የሚገነቡ ሰባት የገጠር መንገድ ፕሮጀክቶችን ለማስገንባት ከተቋራጮች ጋር የውል ስምምነት ተፈራረመ።
በሚዛን አማን ከተማ በተከናወነው የፊርማ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተገለጸው፣ ፕሮጀክቶቹ አምስት አዳዲስ መንገዶችን እና ሁለት የጥገና ሥራዎችን የሚያካትቱ ሲሆን፣ በክልሉ በሚገኙ አምስት ዞኖች ውስጥ ተግባራዊ የሚሆኑ ናቸው።
በቢሮው የገጠር ትስስር ለምግብ ዋስትና (RCFSP) ፕሮግራም ማኔጀር አቶ ሰለሞን ቀለመወርቅ እንደገለጹት፣ ለፕሮጀክቶቹ ግንባታ በጠቅላላ 266,769,518 ብር ተመድቧል። የፋይናንስ ምንጩም፦70 በመቶ በዓለም ባንክ፣10 በመቶ በክልሉ መንግሥት፣10 በመቶ በዞን፣ቀሪው 10 በመቶ ደግሞ በየወረዳዎቹ የሚሸፈን መሆኑ ተገልጿል።
ግንባታዎቹ በዳውሮ፣ በሸካ፣ በምዕራብ ኦሞ፣ በቤንች ሸኮ እና በኮንታ ዞን በተመረጡ ወረዳዎች ላይ የሚከናወኑ ሲሆን፣ በዋናነትም የምግብ ዋስትናው የተረጋገጠ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል።
የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የሁሉአቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ዘርፍ ኃላፊ ኢንጂነር ጌዲዮን እስጢፋኖስ በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፣ ፕሮግራሙ በ2017 ዓ.ም. ወደ ሥራ ከገባ በኋላ በስድስት ዞኖች ውስጥ ሰባት ፕሮጀክቶች ተጀምረው ስድስቱን ማጠናቀቅ ተችሏል። አሁን የተፈረሙት ፕሮጀክቶችም በአምስት ወራት ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁ ገልጸዋል።
የቢሮው የትራንስፖርት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ዘመዴ አንዳርጌ በበኩላቸው፣ የፕሮጀክቶቹ የጥራትና የጊዜ ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ አለመሆኑን በማሳሰብ፣ በሥራ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ቢሮው ከተቋራጮች ጋር በቅርበት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
እነዚህ መንገዶች ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት የሚሰጡና የማኅበረሰቡን የትኩረት ተጠቃሚነት በውል የሚያረጋግጡ መሆናቸው በዘገባው ተመልክቷል።
