



የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ጋር በመተባበር በጠቅላላ የሻይ አግሮኖሚ ላይ ለባለሙያዎች በቦንጋ ከተማ ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቋል።
ስለጠናው በጠቅላላ የሻይ አግሮኖሚ እስከ ምርት ዝግጅት፤ የችግኝ ጣቢያ ምስራታና አያያዝ እንዲሁም በዘርፉ በቀጣይ መከተል በሚገባቸው የትኩረት አቅጣጫዎችና መወሰድ በሚገባቸው ጥንቃቄዎች ላይ ያተኮረ ነው።
ሰልጣኞቹ ስልጠናው በዘርፉ የነበረውን ማነቆ ለመፍታት አቅም የሚፈጥር፤ ለዘርፉ ቀጣይ ስራ ምቹ መደላደልና ለዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አንስተዋል።
የስልጠና መድረኩን ያጠቃለሉት የክልሉ ቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩሪያ ሰልጣኞች ከስልጠናው በመነሳት አርሶ አደሮችን በዕውቀትና በክህሎት በመምራት ወደ የሻይ ልማት ዘርፉ በሰፊው ለማቀላቀል ቁርጠኛ እንዲሆኑ አሳስበዋል።
የሻይ ኢንሼቲቭ በአርሶ አደሩ ዘንድ አድስ በመሆኑ ከስልጠና ያገኙትን ግብዓት በተገቢው መንገድ ግንዛቤ በማስጨበጥ የሻይ ኢንሼቲቭ ውጤታማ በማድረግ የአርሶ አደሩንና አልሚዎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ ዋና ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
በመሆኑም ባለፉት ዓመታት በክልሉ በዘርፉ እየመጣ ያለውን ዉጤት ለማስቀጠል ባለሙያዎች ሳይንሱን በመረዳት ወደ ተግባር በመቀየር የገጠር ሽግግርን ለማፋጠንና ለኢንዱስትሪው መሠረት ለመጣል የሻይ ልማት ላይ በትኩረትና በቅንጅት እንዲሰሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር እና የልማት ጥበቃ ዘርፍ ኃላፊ አቶ በላይ ኮጁአብ ለሻይ ልማት ዋናው ግብዓት ችግኝ በመሆኑ ከችግኝ ጣቢያ ምስረታ እስከ ተከላ ማሳ መረጣና አርሶ አደር ልየታ ድረስ በሚደረጉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የዘርፉ ኢንሸቲቭን ስኬታማ ለማድረግ በየደረጃው ያሉ የባለድርሻ አካላት ትኩረት እንደሚሻ አንስተው ባለሙያዎች የወሰዱትን ስልጠና ወደ ተግባር በመቀየር ለውጤታማነቱ መረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በቀረበው ሰነድ ላይ በተሳታፊዎች ሰፋ ያለ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ግልፀኝነት በሚፈልጉ ጉዳዮች ከመድረከና ከአሰልጣኞቹ ተጨማሪ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።
በጌታሁን ግርማ
