
በመጀመሪያው ዙር 11 ወረዳና ከተማ አስተዳደሮች ውስጥ ከ16,000 በላይ ህፃናት ተጠቃሚ ይሆናሉም ተብሏል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ፣ በክልሉ ከፍተኛ የወባ ስርጭት በሚታይባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ህፃናትን ከበሽታው ለመታደግ የሚያስችል አዲስ የወባ መከላከያ ክትባት መስጠት ልጀምር መሆኑን ለደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ዛሬ በሰጠዉ መግለጫ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በሰጡት መግለጫ፣ ይህ ክትባት ህፃናት በበሽታው ከመያዛቸው በፊት የሰውነታቸውን በሽታ የመከላከል አቅም በማሳደግ ከወባ ጋር ተያይዞ የሚመጣን ህመምና ሞት ለመቀነስ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ክትባቱ በአለም ጤና ድርጅት (WHO) እና በኢትዮጵያ መድሃኒትና ምግብ ቁጥጥር ባለስልጣን እውቅና የተሰጠው ሲሆን፣ በተለይ መካከለኛ እና ከፍተኛ የወባ ስርጭት ባለባቸው አካባቢዎች እንደ ዋና የመከላከያ ማዕቀፍ አካል ሆኖ ያገለግላል።
ክትባቱ የበለጠ ውጤታማ የሚሆነው መቼ ነው?
አቶ ኢብራሂም እንዳብራሩት፣ ክትባቱ ከሌሎች ነባር የመከላከያ ዘዴዎች ጋር ተቀናጅቶ ሲተገበር ውጤታማነቱ ይጨምራል ያሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል፦በፀረ-ተባይ የተነከሩ የአልጋ አጎበሮችን በአግባቡ መጠቀም፣የቤት ውስጥ ፀረ-ተባይ ርጭት ማስደረግ፣የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን ማጽዳትና ማጥፋት ይገኙበታልም ስሉ ጠቅሰዋል።
ክትባቱ የሚሰጠው እድሜያቸው ከ6 ወር እስከ አንድ ዓመት ለሆኑ ህፃናት ሲሆን፣ ሙሉ በሙሉ በነፃ በጤና ተቋማት ይሰጣል። አንድ ህፃን ለአራት ጊዜያት በመውሰድ ክትባቱን ያጠናቅቃል።
1ኛ ዙር፦ በ6ኛው ወር
2ኛ ዙር፦ በ7ኛው ወር
3ኛ ዙር፦ በ9ኛው ወር
4ኛ ዙር (የማጠናከሪያ)፦ በ15ኛው ወር
ለተሻለ ጥበቃ ሁሉም ህፃናት አራቱንም ዙር ክትባት ሙሉ በሙሉ መውሰድ እንዳለባቸው ቢሮው አሳስቧል።
በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ የወባ ስጋት ካለባቸው ዞኖች የተመረጡ 11 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች በፕሮግራሙ የመጀመሪያ ዙር ተካተዋል። በዚህም በአጠቃላይ 16,411 ህፃናት የክትባቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ።
የሚካተቱት አካባቢዎችም፦ታርጫ፣ ጪዳ፣ ቦንጋ፣ ሺሽንዳ፣ ሚዛን አማን፣ ሲዝ፣ ቴፒ፣ ጀሙ፣ ባቹማ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ኮንታ ኮይሻ እና ቤሮ ወረዳዎች ናቸው።
የክትባት ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሲጀመር፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ደግሞ ቴፒ ከተማ አስተዳደር ቀዳሚ በመሆን መስጠት ጀምሯል። ሌሎች አካባቢዎችም አስፈላጊውን የግብዓትና የሥልጠና ዝግጅት እንዳጠናቀቁ አገልግሎቱን እንደሚጀምሩ ገልጸዋል።
በመጨረሻም የቢሮ ኃላፊው አቶ ኢብራሂም ተማም “ወላጆችና አሳዳጊዎች እድሜያቸው ከ6 እስከ 11 ወር የሆኑ ህፃናትን በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ጤና ጣቢያ፣ ጤና ኬላ ወይም ሆስፒታል በመውሰድ ይህንን አዲስ እድል እንዲጠቀሙ” ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
