ተቋሙ በአጭር ጊዜ ያከናወናቸውን አበረታች ተግባራትን አጠናክሮ ሊያስቀጥል ይገባል_ክብርት ወ/ሮ ፀሀይ ዳርጫ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ የ2017 በጀት አመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም በክልሉ ምክር ቤት የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተገምግሟል።

ምክር ቤቱ በምክር ቤቱ የፀደቁ ደንቦችን፣ መመሪያዎችን፣ በጀቶችን፣ ዕቅዶችንና የአሰራሮችን ተፈፃሚነት በመገምገም የተሻለ አፈፃፀም እንዲኖር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም ወ/ሮ ፀሀይ አስረድተዋል።

በዚህም የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ በተደራጀ በአጭር ጊዜ ተቋሙን በሰው ሀይልና በግብአት ከማደራጀት እንዲሁም ስራ በጀመረበት የድህረ ገፅና ማህበራዊ ሚዲያ ዘርፍ ያከናወኗቸው ተግባራት እጅግ አበረታች እንደሆነ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ምክትል አፌ ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ፀሀይ ዳርጫ ገልጸዋል።

ለውጤቱ የተቋሙ አመራር ያሳዩት ቁርጠኛነትና የባለሙያዎች ትጋት የሚደነቅና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባ እንደህነም አስረድተዋል።

ቅንጅታዊ ስራዎችን በማጠናከር ተቋሙ በሚፈለገው ደረጃ ተልዕኮን እንዲወጣ ምክር ቤቱ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

ምክትል አፌ ጉባኤዋ ተቋሙ ከማህበራዊ ሚዲያ በተጨማሪ በቴሌቪዥንና በሬድዮ መረጃዎችን ማሰራጨት እንዲጀምር ሁሉም የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሚዲያ ኔትወርኩ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መንግስቱ መኩሪያ በበኩላቸው ምክር ቤቱ አፈፃፀምን ከመገምገም ባሻገር በርካታ ድጋፎችን በመስጠት ለተቋሙ ውጤታማነት እያደረገ ያለው ጥረት የሚያስመሰግን እንደሆነ ተናግረዋል።

አቶ መንግስቱ አክለውም ተቋሙ የሚዲያ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ በጀትና የቴክኖሎጂ ግብአቶችን የሚጠይቅ ስለሆነ አስፈላጊ ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

የሚዲያ ኔትወርኩ ምክትል ስራ አስኪያጅና የይዘት ዘርፍ ሀላፊ ዶ/ር ካሳሁን ወዳጆ ምክር ቤቱ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው ሚዲያው ጥራት ያላቸውን መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ለማድረስ ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አንስተዋል።

በግምገማ መድረኩ የሚዲያ ኔትወርኩ የስራ ሀላፊዎችና የማኔጅመንት አባላት ተገኝተዋል ሲል የደ/ም/ኢ/ሚ/ኔ ዘግቧል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *