




አቶ ፎላ ጃርሶ በዳውሮ ዞን ሎማ ቦሳ ወረዳ፣ የሱቦ ቱለማ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ፥ ከአመታት በፊት ግንባር ቀደም የአከባቢው አርሶአደር ነበሩ።
አቶ ፎላ በተሰማሩበት የግብርና መስክ ውጤታማ በመሆን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ምርታማነትን በማሳደግ ዛሬ ላይ ከሞዴል አርሶ-አደርነት ወደ አልሚ ባለሀብትነት ተሸጋግረዋል።
በአካባቢው ለኢንቨስትመንት በወሰዱት መሬት የተለያዩ ሰብሎችን ቢያመርቱም የሚፈለገው ውጤት ባለመገኘቱ ካዛቫን (cassava) ለማምረት መወሰናቸውን የሚገልጹት አቶ ፎላ አሁን ላይ በካዛቫ ምርት ውጤታማ እንደሆነ ይናገራሉ።
ካዛቫ በደቡቡ የሀገሪቱ አከባቢ በስፋት የሚታወቅ ሥራስር ምግብ ሲሆን በቅርቡ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ከተለመዱት የጤፍ እና ሌሎች እህሎች ላይ ተጨምሮ በእንጀራ መልክ እንዲቀርብ ፈቃድ ማግኘቱ ይታወሳል።
ካዛቫ የአየር ለውጥን መቋቋም የሚችል ሥራስር በመሆኑ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ተመራጭ የምግብ አይነት ነው ያሉት አቶ ፎላ፥ በአከባቢው ገበያ ምርቱ በኪሎ እስከ 60 ብር እንደሚሸጥ አስረድተዋል።
የካዛቫ ምርት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ፎላ፥ ከዋናው ምርት (ስር) በተጨማሪ ግንዱ ተቆርጦ የሚተከል እንዲሁም ተረፈ ምርቱ ደግሞ ለእንስሳት መኖነት እንደሚውልም ተናግረዋል።
በ18 ወራት ለምግብነት የሚውለው የካዛቫ ምርት በአከባቢው በተለምዶው እንደ ሌሎች ስራስር ምግቦች ተቀቅሎ የሚበላ ሲሆን አሁን አሁን ደርቆ በዱቄት መልክ ከሌሎች እህሎች ጋር ተቀላቅሎ ለምግብነት በስፋት እየዋለ ይገኛል ብለዋል።
ከአንድ ሄክታር በአማካይ ከ1ሺህ 500 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚገኝ የሚገልጹት ባለሀብቱ፥ በቀጣይ ምርቱን በስፋት በማምረት አቀነባብሮና ዕሴት ጨምሮ ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ዕቅድ እንዳላቸውም ተናግረዋል።
ኢንቨስትመንቱ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ እንደሆነ የገለጹት አቶ ፎላ ጃርሶ፥ ቀጣይነት ባለው መልኩ ውጤታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የመንግሥት ድጋፍና ክትትል እንዲጠናከር በአንክሮ ጠይቀዋል።
አቶ ፎላ በቀደሙት ጊዜያት በአከባቢው ስመጥር ሞዴል አርሶአደር እንደነበሩ በማስታወስ አሁን ለደረሱበት ደረጃ የመንግሥት ድጋፍ እንዲሁም የባለሙያ ምክር ተግባራዊ ማድረግ በመቻላቸው ውጤታማ እንደሆኑም አስረድተዋል።
የካዛቫ ምርት በባህሪው ከፍተኛ የፀሃይ ጫናን መቋቋም የሚችልና የምግብ ዋስትና በቤተሰብ እንዲሁም በማኅበረሰብ ደረጃ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል አቅም እንዳለው የገለጹት ባለ-ሀብቱ አቶ ፎላ፥ ምርት በማቀነባበር በተሻለ መልኩ ለገበያ ተደራሽ ለማድረግ የብድር አማራጮች መመቻቸት አለበት ብለዋል።
በመጨረሻም ይኼንን የካዛባን ምርት በአብዛኛው በሀገርቱ ቆላማው አካባቢ ማስፋት ቢቻል መንግስት የግብርናውን ምርት ከማሳደግ አኳያና የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ ከተሰጠው ትኩረት አንጻር የተሻለ መፍትሔ በመሆኑ በሁሉም አካባቢ የማስፋፋት ሥራ ቢሰራ የተሻለ ውጤት እንደሚገኝ አስተያየታቸውን በመስጠት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
