የእንስሳት ዝሪያን በማሻሻል የወተት ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለጸ።

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የአርብቶ አደር እና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ ከቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ጋር በመተባባር ሰው ሰራሽ የእንስሳት ማዳቀል ስራ በማጂ ወረዳ አስጀምሯል።

በማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የቢሮ ኋላፊው አቶ መቱ አኮ መንግሥት ከእንስሳት ቁጥር ይልቅ ጥራትና ምርታማነት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በመሆኑም በሰው ሰራሽ ዘዴ ላሞችን በማዳቀል ምርታማነታቸው የተረጋገጠ እና ጥራት ያላቸውን ላሞች በማብዛት የአርብቶ አደሩን ኑሮ ማሻሻል እንደሚገባም አሳስበዋል።

ለዚህም ስኬት የአርብቶ አደር እና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ ከቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ጋር በመተባባር ሰው ሰራሽ የእንስሳት ማዳቀል ተግባርን በይፋ ማስጀመሩን ተናግረዋል።

ይህም ውጤታማ እንዲሆን ላሞችን ማዳቀል ብቻ ሳይሆን ለተዳቀሉት ላሞች የሚሆን የጤና አጠባበቅ እና መኖ የማዘጋጀት ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

በቢሮው የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ደረጀ በቀለ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የአርብቶ አደሩን ሕይወት ለመቀየር በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም በ2018 በጀት ዓመት በክልሉ ውስጥ በማጂ፣ ጎልዲያ፣ ሜኤኒት እና ጎባ ወረዳዎች ባጠቃላይ 4 መቶ 50 ላሞችን በሰው ሰራሽ ዘዴ ለማዳቀል ማቀዱን ተናግረዋል።

በምዕራብ ኦሞ ዞን ማጂ ወረዳ ማጂ ቱም ከተማ በይፋ የተጀመረው 150 ላሞችን የማዳቀል ተግባር መሆኑንም ገልጸዋል።

“የተሻሻለ የዛሬ ጥጃ የነገ ላም በእያንዳንዱ አርብቶ እና አርሶ አደር ቤት” በሚል መሪ ሃሳብ ፕሮግራሙ መጀመሩን የጠቀሱት አርብቶ አደር እና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ የእንስሳት ዝሪያና የወተት ሀብት ልማት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ተገኝ ወርቅ ሳልልህ እንስሳትን በቁጥር ሳይሆን በጥራት ማብዛት ይገባል ብለዋል።

ይህም አርብቶ እና አርሶ አደሩን የሌማት ትሩፋት ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ አቅሙን የሚያሳድግ በመሆኑ ሁሉም ለውጤታማነቱ መረባረብ እንዳለበት አሳስበዋል።

በመርሃ ግብሩም የክልል፣ የምዕራብ ኦሞ ዞን፣ የማጂ ወረዳ እና የማጂ ቱም ከተማ አስተዳደር አመራሮችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል ሲል የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *