የዘንድሮ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል የክልሉ ብዝሃ ማዕከል በሆነችው በታርጫ ከተማ ተከብሯል።

Spread the love

129ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።

የበዓሉ ክብር እንግዳ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም የዓድዋ ድል የመላው የጥቁር ህዝቦች ድል ነው በማለት ይህ ድል ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሀገር እንድትሆን ያስቻለ ሲሆን በዚህ ድል የተሳተፉ የኢትዮጵያ ጀግኖች መሰዋዕትነት የሚረሳ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል።

በዓሉ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ህዝቦች የአርበኝነት ታሪክ መሆኑን የገለፁት አቶ ኢብራሂም ቀደምት አባቶቻችን የሰሩትን ገድል አሁን ያለው ትውልድ በትብብርና በትጋት ሀገራችንን ወደ ሁለተናዊ ብልፅግና ለማድረስ መሰራት አለብን ስሉ አሳስበዋል።

በህብረ ብሔራዊነት አንድነትን በማጠናከር ኢትዮጵያን በአፍሪካ ብሎም በዓለም ከፍ ማድረግ ይጠበቅብናል ስሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አክሊሉ ለማ የዕለቱን የመወያያ የውይይት ሰነድ አቅርበዋል።

ከውይይቱ ሰነድ መነሻ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ በበኩላቸው ባርነትን እና ቅኝ ግዥነትን ታግሎ ያሸነፈ የሀገርን ሉዓላዊነትን ያስጠበቀ አርበኛ ትውልድ ለኢትዮጵያ መኖሩን ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የዛሬው ትውልድ ዳግም አድዋን በመድገም ህዳሴን በመገንባት አሁንም በኢኮኖሚ አሸናፊነት እና ህብረ ብሄራዊነትን በማጠናከር አንድነትን ማስጠበቅ አለበት ሲሉም ገልጸዋል።

የቅድመ አያቶቻችንና አባቶቻችን በራስ መተማመን በደም መሰዋዕትነት ያመጡትን ታሪክ ለማስቀጠልና ዓድዋ ላይ የታየው ተጋድሎ በልማት ዘርፍ እንዲደገም በጋራ ልንረባረብ ይገባል ያሉት የዳውሮ ዞን ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባል የሆኑት አቶ ግርማ ግዛው ናቸው።

የዳውሮ ዞን ምክርቤት ዋና አፈጉባኤ አቶ ዳዊት ሚኖታ አሁን የሚያስፈልገን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ማስከበር ያስፈልጋል በማለት ሁሉም ዜጋ ለጋራ ብልፅግና እንደ ህዳሴ ግንድ የድርሻውን እንድወጣ አሳስበዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም አድዋን በዓላማ ፅናት ማሳየት አለብን በማለት በገጠርና በከተማ ኮርደር ልማት፣ በልማት ትሩፋት እና ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት ሥራ መስክ በውጤታማነት በመሥራት በአንድነት ያለምንም ልዩነት ተግባብተን መሥራት አለብን ስሉ ገልጸዋል።

129ኛው የዓድዋ ድል መታሰብያ በዓሉ በፖሊስ ሠራዊት ትርዕት፣ በሰርከስ ስፖርት፣ በዳውሮ ባህል ባንድ እና እንዲሁም በተለያዩ ኩነቶች በመታጀብ ተከብሯል።

በመታሰቢያ በዓሉ በታርጫ ማዕከል የሚገኙ የክልል መዋቅር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ መንግሥት ሠራተኞች እንዲሁም የዞን መዋቅር እና የአባት አርበኞች ተገኝተውበታል ሲል የዳውሮ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *