




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና ትራንስፖርትና የመንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋጂዋ ሳፒን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የሚዛን አማንን የኮሪደር ልማት ሥራ ጎብኝተዋል።
የክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ትራንስፖርትና የመንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋጂዋ ሳፒ እንደገለፁት የኮሊደር ልማት እንደ ሀገር ስራ ከተጀመረ ወዲህ በክልሉ መዘግየት ቢኖርም ህዝቡና አመራሩ በመቀናጀት በሚዛን አማን ወደ ስራ እንዲገባ መደረጉን ተናግረዋል።
በሚዛን አማን ከተማ አንድ ኪሎሜትር የሚሸፍን በ3 ተቋራጮች እየተሰራ ያለው ስራ እሰይ የሚያስብል መሆኑን ጠቁመዋል።
አቶ ፋጂዋ ከክልሉ ፕሬዚዳንት ጋር በመሆን ከዚህ ቀደም የኮሪደር ልማት ሥራውን ካየነው ወዲህ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ማጠናቀቅ የሚያስችል ሁኔታ ላይ መሆኑን በጉብኝቱ አይተናል ሲሉ ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማት ስራው ቀንና ማታ በመስራት የስራን ባህል እየቀየረም መሆኑን ተናግረዋል።
በከተማው የኮሪደር ልማት ስራውን ማስፋት ላይ የህብረተሰቡና የአመራሩ ቅንጅት ከፍተኛ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በክልሉ ባሉ ሁሉም ከተሞች ልምዶችን በመውሰድ ውብ እና ማራኪ ከተማ እያደረጉ መሄዱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን መንገሻ በበኩላቸው የኮሪደር ልማት ሥራው አበረታች መሆኑን ጠቁመው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የዞኑ ድጋፍ እንደማይለይም ተናግረዋል ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።
