በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከ107 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል፦ ግብርና ሚኒስቴር

Spread the love

በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በዘር ከተሸፈነው 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት እስካሁን ከ107 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ኢሳያስ ለማ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ በርካታ ተግባራት እያተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

በእነዚህ ተግባራትም በግብርናው ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እየተቻለ መሆኑን ጠቁመው በስንዴ ልማት ላይ በተሰራው ስራ የተገኘው ውጤት ለዚህ ትልቅ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በዚህ አመትም ምርታማነትን ለማሳደግ በበጋ መስኖ ልማት 4ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማረስ እቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡

ከተያዘው ዕቅድ ውስጥ 3ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑንና ከእዚህ መካከል እስካሁን 107 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት መሰብሰቡን ጠቅሰዋል፡፡

የመስኖ ስንዴ ምርት አሰባሰብ በሚቀጥሉት 15 ቀናት ውስጥ ወቅቱን ጠብቆ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በመስኖ ስንዴ ልማቱ ዋና ዋና የበልግ አብቃይ አካባቢዎች መደበኛው ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ በመጣሉ በቂ የስንዴ ምርት እንዲሰበሰብ አስቻይ ሁኔታ መፈጠሩን አስታውቀዋል።

በተያዘው ዓመት የበልግ ወቅት በቆሎ፣ ማሽላ፣ ቦሌቄ፣ የስንዴና የገብስ ምርቶች በስፋት የሚዘሩበት ወቅት መሆኑን መሪ ስራ አስፈጻሚው ጨምረው ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በተከናወኑ የግብርና ስራዎች በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ ውጤት እያስገኘ መሆኑን አስረድተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *