
ኢትዮጵያ በዲጂታል ስርዓት የታገዘ የግምገማ ስርዓትን በመከተል በመረጃ ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ ውሳኔዎችን እየሰጠች እንደምትገኝ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ተናገሩ።
የአፍሪካ የግምገማ ማህበር 25ኛ የምስረታ በዓሉን ምክንያት ያደረገ ውይይት በአዲስ አበባ እያካሄደ ይገኛል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ ኢትዮጵያ ለምትተገብራቸው ፖሊሲዎችና የልማት ዕቅዶች ውጤታማነት ጠንካራ የግምገማ ስርዓት ዘርግታ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ብሔራዊ የልማት ዕቅዶችን ከአጀንዳ 2063 እና ዘላቂ የልማት ግቦች ጋር በማስተሳሰር እየሰራች መሆኗንም ተናግረዋል።
የሚተገበሩ የልማት ዕቅዶችና የሚሰጡ ውሳኔዎች በጥናትና መረጃ ላይ የተመሰረቱ መሆኑን በመጠቆም ለዚህም በቴክኖሎጂ የታገዙ ጠንካራ የግምገማ ተቋማትን በማደራጀትና ሙያተኞችን በማብቃት እየተሰራ እንደሚገኝ አክለዋል።
ተግባራዊ የሚደረጉ ዕቅዶችና ስትራቴጂዎች ላይ የሚደረጉ ግምገማዎች ለዜጎች የሚሰጠውን አገልግሎትና የልማት ተጠቃሚነት ለማሻሻል ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የአፍሪካ ህብረት የስትራቴጂክ ዕቅድና ትግበራ ዳይሬክተር ቦቶ ከባቦንይ በበኩላቸው በአጀንዳ 2063 የተያዙ የልማትና የሰላም ዕቅዶችን ለማሳካት ጠንካራ የግምገማ ስርዓት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
የአፍሪካ ሀገራት ነባራዊ ሁኔታዎችን ከአጀንዳ 2063 ጋር በማስተሳሰርና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ስትራቴጂ በማውጣት ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በዚህም ልማትን ለመተግበር የሚደረጉ ግምገማዎች መሰረታዊ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በአፍሪካውያን ሙያተኞች የሚደረጉ ግምገማዎችን በማጠናከር የአፍሪካውያንን ችግር በአፍሪካውያን የመፍታት ባህል የበለጠ ሊጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የአፍሪካ የግምገማ ማህበር በአጀንዳ 2063 የመጀመሪያ 10 አመት የትግበራ ጊዜ ሙያዊ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጰው በቀጣይም እገዛውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የፓን አፍሪካ የግምገማ ማዕከል ለመሆን እየሰሩ እንደሚገኙ የተናገሩት ደግሞ የአፍሪካ የግምገማ ማህበር ፕሬዝዳንት ሚሼ ኦድሪጉ ናቸው።
በቴክኖሎጂ የታገዙ የግምገማ ስልቶችን በመጠቀም በአህጉሪቱ የሚተገበሩ የልማት ዕቅዶችን ለማሳካት መስራት ወሳኝ በመሆኑ ማህበሩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችንና ሙያዊ ምክረ ሃሳብ በመስጠት ከሀገራት ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው የማህበሩ 25ኛ አመት የምስረታ በዓል ላይ ከአፍሪካና ሌሎች ሀገሮች የተውጣጡ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የግምገማ ባለሙያዎች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።
ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት በሚቆየው መርሃ ግብር በአህጉሪቱ እየተተገበሩ የሚገኙና ቀጣይ የሚተገበሩ የልማት እቅዶችን ለማሳካት ትብብርን ማጠናከር፣ ወጣት የግምገማ ባለሙያዎችን ማበረታታት፣ ማህበሩ ያሳካቸውን ውጤቶች መገምገም እንዲሁም ክፍተቶችን መለየትና ሌሎች ሁነቶች እንደሚከናወኑ ይጠበቃል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
