የውጭ ዜጎች የቋሚ ንብረት ባለቤትነት ረቂቅ አዋጅ ቢጸድቅ የሚያስገኘው ጠቀሜታ ምንድን ነው?

Spread the love

65 ዓመታትን የስቆጠረውንና የውጭ ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለይዞታ መሆን እንዳይችሉ ያደረገውን አዋጅ ለማሻሻል ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱ ይታወቃል።

በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ውይይት እያካሄደ ነው።

የፍሕ ሚኒስቴር እና የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በውይይቱ ላይ ተገኝተዋል።

አዋጁ መሻሻሉ ስለሚኖረው ጠቀሜታ የፍትሕ ሚኒስትሯ ሀና አራዓያሥላሴ በዚህ ወቅት አብራርተዋል።

የውጭ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የውጭ ካፒታልን ሥራ ላይ እንዲያውሉ ማበረታታት፣ እየሰፋ የመጣውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት እና አቅርቦት ሚዛን በተገቢው መንገድ ማስጠበቅ፣ የቤት ልማት እና ተደራሽነትን ይበልጥ ማነቃቃት ከአዋጁ መሻሻል የሚጠበቁ ውጤቶች ናቸው ብለዋል።

እረቂቅ አዋጁ የተለያዩ ግዴታዎችንም አስቀምጧል፤ የውጭ ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ሲሆኑ የሊዝ፣ የቤት ግዢ፣ የግንባታ ፈቃድ፣ ወይም ተያያዥ የመንግሥታዊ አገልግሎት ክፍያዎችን በኢትዮጵያ ተቀባይነት ባለው የውጭ ምንዛሬ ብቻ እንዲከፍሉ የሚለው አንደኛው ግዴታ ነው።

የውጭ ዜጋ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት መሆን የማይችልባቸው ልዩ ቦታዎች ወይም የድንበር አካባቢዎች በመመሪያ እንደሚወሰኑም ረቂቁ ላይ ተቀምጧል።

በመንግሥት ቀጥተኛ ድጎማ ለዜጎች በሚሠሩ የጋራ መኖሪያ ሕንፃዎች ውስጥ የውጭ ዜጎች የንብረት ባለቤት መሆን እንደማይችሉም በረቂቅ አዋጁ ተቀምጧል።

የውጭ ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ ለመሆን ከአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋም ወይም ምንጭ ገንዘብ መበደር ወይም ካፒታል ማሰባሰብ እንደማይችሉም ረቂቁ ላይ ሰፍሯል።

የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ መሆን የሚፍለጉ የውጭ አገር ዜጎች በቅድሚያ ከሚኒስቴሩ ፈቃድ ማግኘት እንዳለባቸው ረቂቁ አመልክቷል።

በረቂቅ አዋጁ ላይ መሻሻል አለባቸው የሚሏቸውን ነጥቦች ቋሚ ኮሚቴዎቹ አንስተው ውይይት እየተደረገባቸውም ይገኛል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *