ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ማንሰራራት የተገለጠበት ብሔራዊ ሀብታችን ነው፦ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

Spread the love

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አባቶቻችን ኪሳቸውን ፈትሸው፣ እናቶቻችን መቀነታቸውን ፈትተው ጥሪት ያፈሰሱበት እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊት አባላት መስዋዕት የሆኑለት ብሔራዊ ሀብታችን ነው ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

የሕዳሴ ኮር ሦስተኛ ዓመት የምሥረታ በዓል “ሕዳሴን በሕዳሴ ኮር” በሚል መሪ ሐሳብ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በተገኙበት ተከብሯል።

በተጨማሪም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ፣ የምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል መሠለ መሰረት፣ ጄነራል መኮንኖችና የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በክብረ-በዓሉ ላይ ተገኝተዋል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በክብረ-በዓሉ ላይ ባሰሙት ንግግር፥ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ማንሰራራት የተገለጠበት ብሔራዊ ሀብታችን ነው ሲሉ ገልጸውታል።

የመከላከያ ሠራዊቱ የኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ሀብት የሆነውን የታላቁ የህዳሴ ግድብን ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ የመጠበቅ ተልዕኮውን በብቃት በመፈጸም ላበረከተው አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *