መከላከል በምንችላቸው ምክንያቶች የእናቶች ህይወት እንዳያልፍ ሁሉም አካላት የድርሻቸውን መወጣት ይገባቸዋል፦የክልሉ ጤና ቢሮ

Spread the love

መከላከል በምንችላቸው ምክንያቶች የእናቶች ህይወት እንዳያልፍ ሁሉም አካላት የድርሻቸውን መወጣት እንደሚገባቸው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ አሳሰበ።

ቢሮው “ፈጠራና ዘላቂ ፋይናንስ ለጤናማ እናትነት” በሚል መሪ ቃል የጤናማ እናትነት ወር ንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።

በንቅናቄ መድረኩ የተገኙት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም፤ መከላከል በምንችላቸው ምክንያቶች እናቶች ላይ ሊደርስ የሚችለውን ሞት በመከላከል ሀላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

በተለይ ደግሞ ለነፍሰ ጡር እናቶች የጤና አገልግሎቶች ጥራታቸውን የጠበቁና ተደራሽነታቸውን በማረጋገጥ በአቅራቢያቸው አገልግሎቱን እንዲያገኙ ማድረግ አለብን ብለዋል።

የማቆያ ጣቢያዎችን በማዘመን ለእናቶች ምቹና ማራኪ በማድረግ በጤና ጣቢያዎች የሚሰጠውን የወሊድ አገልግሎት ምጣኔ በማሳደግ በእናቶችና ህፃናት ላይ ሊደርስ የሚችለውን የሞት ምጣኔ ለመቀነስ ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

እናቶች በአቅራቢያቸው የጤና አገልግሎቶችን በማግኘት በሰለጠኑ ባለሙያዎች መውለድ እንዲችሉ የግንዛቤ ስራዎች ያለማቋረጥ በመተግበር ሀገራችን የያዘችው እቅድ ከግብ እንዲደርስ መስራት አለብን ያሉት ደግሞ የቢሮው ምክትልና የፕሮግራሞች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሀይሌ ዘውዴ ናቸው።

የጤናማ እናትነት ወር ንቅናቄ አላማው በዋናነት የተለያዩ የግንዛቤ እንቅስቃሴ መድረኮችን በመፍጠር ጥራት ያለውን የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን የሚያጠናክሩ ፈጠራና ዘላቂ የፋይናንስ አቀራረቦችን በመዘርጋት መከላከል የሚቻለውን የእናቶችን ሞት መቀነስ መሆኑን በቢሮው የእናቶች፣ ህፃናት፣ አፍላ ወጣቶች እና ስነ-ምግብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መሠረት ወ/ማርያም ተናግረዋል ሲል ደሬቴድ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *