በግማሽ ዓመቱ በብዙ መልኩ ውጤት የተመዘገበበት እና የአመራር የማስፈፀም አቅም እያደገ የመጣበት ነው -አቶ ፍቅሬ አማን

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርጫፍ ጽ/ቤት የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የፓርቲ ስራዎች አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።

በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት የተከናወኑ የፓርቲ ስራዎች አፈፃፀም ሪፖርት እና የቀጣይ የትኩረት ግቦች ላይም ውይይት ተደርጓል።

የ2017በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ተቋማት የዕውቅናና ማበረታቻ ሽልማት በማበርከት ደካማ አፈጻጸም ላስመዘገቡት ተቋማት እና ግለሰቦች ላይ የእርምት እርምጃ ተወስዶ ማስተካከያ በማድረግ እና በ2018 በጀት ዓመት ግቦች ላይ መግባባት ተፈጥሮ ወደ ተግባር በመገባቱ በሁሉም ዘርፎች ስራዎችን በውጤት የመለካት ሁኔታ እያደገ መምጣቱም በሪፖርቱ ተመላክቷል።

በተለይ የህብረተሰቡን አንገብጋቢ ችግሮችን በመለየት ከተሰሩት ተግባራት መካከል በጤና ተቋማት የሚስተዋሉ የመድኃኒት አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት በየደረጃው ባለው አስተዳደር በልዩ ሁኔታ እየተወሰነ አቅርቦቱን ማሻሻል መቻሉ፣በመንገድና ትራንስፖርት ዘርፍ ህዝቡ በቅሬታ መልክ የሚያነሳቸው ችግሮችን በመለየት የእርምት እርምጃ መወሰዱን እንዲሁም በህገወጥ ንግድ ላይ ቁጥጥር የማጠናከር ሥራ መሠረቱም ተጠቅሷል።

የኑሮ ውድነትን ለመቀነስና ገበያን ለማረጋጋት 36 የሰንበት ገበያዎችን ማቋቋም መቻሉን፣33 ኬላዎችን ሙሉ በሙሉ ማንሳት መቻሉ እንዲሁም የሌማት ትሩፋት እና ሜካናይዜሽን በማስፋፋት የምርት አቅርቦትን በማሳደግ በዘርፉ ውጤታማ ተግባር ማከናወን እንደተቻለም በሪፖርቱ ተገልጿል።

በመድረኩም የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ፣በተለያዩ አካባቢዎች ለሚሰሩ የብልፅግና ፓርቲ ህንፃ ግንባታዎች ሀብት አሰባሰብ ሂደት ያለበት ደረጃ፣ የፋይዳ መታወቂያ፣ የወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ፣የቀጣይ ምርጫ ስራዎች፣ለህዝብ ቅሬታ መፍትሔ መስጠት፣ የመንግሥት ኢኒሼቲቮችን ከዳር ማድረስ ኢንዲሁም የመንግስት እና የፓርቲ ተግባራትን አቀናጅቶ በንቅናቄ መምራት የሚሉ የትኩረት ነጥቦች ላይ በስፋት ውይይት ተደርጓል።

የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ቅርጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን እንደተናገሩት፣አመራሩ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እና መልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ውስጥ የማስፈጸም አቅሙ እያደገ መምጣቱን ገልጸው ባለፉት 6 ወራት በመንግስትና ፓርቲ የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን አስረድተዋል።

በተለይ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ተደራሽ በማድረግ፣ህዝባዊ ውይይት በማድረግ እና ለቀጣይ ምርጫ ዝግጅት መፍጠር እንዲሁም የመንግስት ኢኒኒሼቲቭ ትግበራ እንዲሁም ፓርቲ ህንፃ ግንባታ ለማስጀመር የተከደበት ሂደት ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

በግማሽ ዓመቱ በብዙ መልኩ ውጤት የተመዘገበበት እና የአመራር የማስፈፀም አቅም እያደገ የመጣበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው በቀጣይ ከዚህ በበለጠ መልኩ በመስራት የመንግሥት እና የፓርቲውን ራዕይ ከዳር ማድረስ እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።

በጽ/ቤቱ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ነጋ አበራ በበኩላቸው፣ባለፋት 6ወራት ጠንካራ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ተግባር በመግባት እንዲሁም የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል በማደረግ በሁሉም ዘርፎች የተመዘገበውን ውጤት ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

የፓርቲው እሳቤ መሬት ወርዶ በህዝብ ዘንድ ውጤት ማምጣት እንዲያስችል ለማድረግ፣የአመራር እና አባላት አስተሳሳሰብ ግንባታ ለማሳደግ እና የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተደረገው ተሳትፎ ስኬታማ ተግባራትን ማከናወን መቻሉን አስረድተዋል።

በመድረኩ የቀጣይ የትኩረት ግቦች ላይም አቅጣጫ ተቀምጧል።

በዚህም የሠላም እና ፀጥታ ሁኔታን ማጠናከር፣የልማትና ኢኮኖሚ ነፃነት ንቅናቄ፣መልካም አስተዳደርና ገበያ ማረጋጋት፣የሀብት አሰባሰብ አቅም ማሳደግ፣ወጣቶችና ሴቶችን አቅም ማጎልበት፣የ2018 ምርጫን ማሳካት፣የውስጥ ትግሉን ማጠናከር፣የህዝብ ጥያቄዎችን መመለስ እንዲሁም የመረጃ አያያዝና የድጂታል መታወቂያ ላይ በትኩረት እንደሚሰራም አቅጣጫ ተቀምጧል።

በካሳሁን አሰፋ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *