



የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት በ2018 በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት የክልሉን ከተሞች የቦታ አጠቃቀምና ሥርዓታዊ ዕድገት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ስትራቴጂካዊ ተግባራትን ማከናወኑን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ኃይሌ አስታውቀዋል።
በበጀት ዓመቱ ባለፉት 6 ወራት ኢንስቲትዩቱ ለማዘጋጀት ካቀዳቸው 15 የፕላን ዓይነቶች መካከል 14ቱ ተጠናቀው ለተፈጻሚነት ዝግጁ መደረጋቸውን ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
የከተማ ፕላን ዝግጅት ሂደት ውስብስብና ሳይንሳዊ ትንታኔ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ኢንስቲትዩቱ የከተሞችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ሁኔታዎች ያገናዘቡ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱንም ገልጸዋል።
ባለፉት 6 ወራት በክልሉ ለሚገኙ 4 ከተሞች መሠረታዊ ፕላኖች መዘጋጀታቸውን የጠቀሱት አቶ ፀጋዬ፣ እነዚህ ፕላኖች የከተሞችን የመሬት አጠቃቀም፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታና የአረንጓዴ ልማት ሚዛን ለመጠበቅ እንዲሁም ከተሞች ያለ ፕላን በዘፈቀደ እንዳይስፋፉ ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በማሻ ከተማ አንድ የሰፈር ልማት ፕላን (NDP) እንዲሁም 5 የከተሞች የቦታ ደረጃ ጥናትና 4 ስኬች ፕላኖች ተዘጋጅተው መጠናቀቃቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ሚዛን አማን ከተማ በዚህ ረገድ ፈር ቀዳጅ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች ያሉት አቶ ፀጋዬ ኃይሌ፤ በአማካሪ ድርጅት አማካኝነት 4 የሰፈር ልማት ፕላኖችና የከተማ ዲዛይን ሥራዎች እየተካሄዱ መሆናቸውንም ገልፀዋል።
በተመሳሳይም የቦንጋ ከተማ አጎራባች የነበሩ የኡፋና የውሽውሽ አካባቢዎችን ወደ ከተማዋ መዋቅር በማካተት፣ ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር መዋቅራዊ ፕላንና ሁለት የሰፈር ልማት ፕላኖች ዝግጅት ተጀምሯል ነው ያሉት።
የፕላን ዝግጅት ብቻውን የከተሞችን ስብዕና መቀየር እንደማይችል የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የተዘጋጁ ፕላኖች በተግባር መተግበራቸውን ለማረጋገጥ በ9 ከተሞችና በ8 ገጠር ማዕከላት የፕላን አፈጻጸም ክትትልና ግምገማ መደረጉን አስረድተዋል።
በዚህ ሂደትም በበጪ፣ ፊዴ፣ ዋካ፣ በታርጫና በግዝመሬት ከተሞች የታዩ የፕላን ጥሰቶች ተለይተው የማስተካከያ እርምጃዎች መወሰዳቸውንም ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ኢንስቲትዩቱ የ4 ከተሞችን የአስተዳደራዊ ወሰን ጥናት ማጠናቀቁን የገለጹ ሲሆን ይህም ከተሞች ያላቸውን የመሬት ሀብት በግልጽ አውቀው እንዲያለሙና ከአጎራባች አካባቢዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት በሕግ እንዲመራ ያግዛልም ብለዋል።
በአጠቃላይ የኢንስቲትዩቱ የስድስት ወራት አፈጻጸም በክልሉ እየታየ ያለውን ፈጣን የከተሞች ዕድገት በዘመናዊ ፕላንና በሳይንሳዊ መረጃ ለመምራት የተደረገ ውጤታማ ጉዞ መሆኑም ተገልጿል።
በቀጣይም ቀሪ ሥራዎችን በማጠናቀቅ፣ የፕላን ተገዢነትን በማረጋገጥ ክልሉን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ዕድገት ማዕከል ለማድረግ ተቋሙ ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ኃይሌ ገልጸዋል ።
በፍቅር ከበደ
