#ሪፖርታዥ
ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የሀገሪቱን ምርት (GDP) እስከ 12 በመቶ እንዲያግዝ እየተሰራ ነው:- የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ

ሀገራችን ኢትዮጵያ ዲጂታል ፖሊሲ አርቅቃ ሲትተገብር ቆይታለች፤ ከእነዚህም አንዱ ላለፉት 5 ዓመታት ሲሰራበት ቆይተው ታህሳስ 2018/2028 የተጠናቀቀው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ነው።
በእነዚህ ማዕቀፎች ሲሰሩባቸው ከቆዩት ጉዳዮች ዲጅታል ግብይት፣ ዲጂታል ልማቶች፣ ቴክኖሎጂ መር የመንግስት አገልግሎቶችን በተደራጀ መንገድ ማስከድና መሠረተ ልማቶችን ለመዘርጋት ታቅደው ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘመድኩን ሠለሞን: ባለፉት ዓመታት ዲጂታል ግብይት(cashless transaction) በቴሌ ብር እና ሌሎች ኢንተርኔት ግብይት አማራጮች መሳለጥ መቻሉ ሀገራችን እንደ ቀድሞ የበይ ተመልካች ሳትሆን ዓለም በደረሰበት ደረጃና ፍጥነት ወደ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲትቀላቀል ያደርጋታል ብለዋል።
ያለፉት አምስት ዓመታት ጉዞ ለዲጂታል 2030 መሠረት የጣለ እና ትምህርቶች የተወሰዱበት ነው ያሉት አቶ ዘመድኩን: በቀጣይም አማራጮችን በማስፋት፣ እኩል ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ እንዲሁም በህዝቦችና ተቋማት መካከል መተማመንን የሚፈጥር ዲጂታል ኢኮኖሚ መፍጠር ላይ እምደሚተኮር ጠቁመዋል።
ለእነዚህ ውጥኖች ሁሉ ወሳኝ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን ከማሟላት አንጻር እንደ ሀገር በትኩረት እየተሰራ ሲሆን በክልላችንም 4ኛ ትውልድ ኔትወርክ በሁሉም ወረዳዎች እንዲሁም 5ኛ ትውልድ ኔትወርክ ዝርጋታ በክልሉ ብዝኃ ዋና ከተሞች ለማድረስ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ዲጂታል ኢትዮጽያ ኢኒሼቲቭ ተግባራዊ ሲደረግ ዋናው ግባችን በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ (በ GDP) ላይ ቴክኖሎጂው ያለውን አስተዋፅኦ ከፍ ማድረግ ሲሆን የመንግስት አገልግሎቶችን እርስ በርስ ማስተሳሰር እና Automate ማድረግ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ሀገራችን የዲጂታል ኢንቨስትመንት መዳረሻ እንዲትሆን እስታርት አፕ ከባቢን በማስፋትና በዘርፉ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ በአይሲቲ ፓርኮችና ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ላይ ተሰማርተው ‘GDP’ን እስከ 12 በመቶ እንዲያግዝ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።
አካታች ዲጂታል ኢኮኖሚ መፍጠር ቀዳሚ ስራችን ነው ያሉት ኃላፊው በግብርና፣ በአገልግሎቱ እና በእያንዳንዱ እንቅስቀሴዎች ላይ የሚስተዋለውን የዲጂታል ክፍፍል በማጥበብ የዜጎችን እኩል ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይጠበቃል ብለዋል።
በዚህም በክልላችን ተግባራዊ የሆነው መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት የተገልጋይን እንግልት ከማስቀረት ባሻገር ለዜጎች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት እያቀረበ መሆኑን አውስተዋል።
በቀጣይ ወደ ዞኖችና ከተሞች ላይ አገልግሎቱን ለመዘርጋት በጨረታ ሂደት ላይ ነን ያሉት ኃላፊው እነዚህ የመረጃ መዕከላት (Data base) ከብሔራዊ መረጃ ማዕከል ቋት ጋር ተሳስረው መረጃን ማዕከል ላደረጉ ውሳኔዎችና ልማቶች መሠረት እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል።
ዘመኑ ቴክኖሎጂን አሟጠን እንዲንጠቀም ያስገድደናል ያሉት ኃላፊው ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለመልካም ዓላማ ማዋል በሚያስችል መልኩ ለመገለገል የተቋቋመውን እንስቲትዩት(AI Institute) ከተለያዩ ተቋማት ጋር የሚያቀርባቸውን የበይነመረብ ኮርሶች(5 ሚልዮን ኮደርስ) ኢኒሼቲቭ በክልላችን ለበርካታ ወጣቶች የኢኮኖሚ ምንጭ እየሆነ ነው ብለዋል።
ይኸውም ለወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ ሚና መኖሩን ገልጸው ኢተዮ ኮደርስ ሰልጥነው ሰርቴፍኬት ከወሰዱ በኃላ በይነ መረብ ላይ በፍሪላንሰርነት ሰርተው በውጭ ምንዛሬ የሚከፋላቸው የክልላችን ውስን ወጣቶችን ፈለግ መከተል አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል።
ፋይዳን ጨምሮ ትላልቅ ብሔራዊ ዳታ ማዕከላት፣ ሲቪል ሰርቪሱን ለማዘመን በታሰበው ትልም ኤሌክትሮኒክስ የመንግስት አገልግሎት በቀጣይ ዲጂታል መር አገልግሎቶችን ለመዘርጋት ምቹ መደላደል መፍጠሩን አንስተዋል አቶ ዘመድኩን።
ዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በሁሉም ዜጎች ዘንድ ለማድረስ ፋይዳ መታወቂያ ቀዳሚው መስፈርት ነው ብለው ይኸውም ዲጂታል ግብይት ስርዓት ከማሳለጥ አልፎ ዳታ አስተዳደር ስርዓት ሎዓላዊነትን ለማረጋገጥ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስደው ገልጸዋል።
በሳለፍነው ታህሳስ ወር ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ይፋ መሆኑን ተከትለው እንደ ክልል ከብሔራዊ ግቦች የተቀዳ እስተራቴጂክ ዕቅድ ይዘን ወደ ትግበራ እየገባን ሲሆን በዋናነትም ዲጂታል ሎዓላዊነት ላይ መስራትና ማህበረሰባችንን በዲጂታል ዓለም ተጠቃሚ ማድረግ ላይ ትኩረት አድርገናል ብለዋል ኃላፊው ጨምረው።
በ2030: 70 በመቶ ያህሉ ህዝብ ዲጂታል ዕውቀት እንዲኖረው ከታለመለት ግብ አንጻር እንደ ክልል ሰፊ ንቅናቄዎች እየተደረጉ ሲሆን ለዚሁ ግብ ቀዳሚ የሆነውን 5 ሚልየን ኮደርስ ስልጠና ላይ እንዲመዘገቡና ሰልጥነው እንደ ቀደሙት ወጣቶች የበይነ መረብ ስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሰፊ ጥረት እየተደረገ ያሉት ኃላፊው በተለያዩ ንቅናቄዎች ከ 10 ሺ በላይ ሰዎች ተመዝግበው መሰልጠን የጀመሩት ሲሆን ከ 7ሺህ 600 በላይ የሚሆኑት ሰርቴፊኬት እንዳገኙ ገልጸዋል።
ሌላኛው የዚሁ ኢኒሼቲቭ ግብ ሲቪል ሰርቪሱን ትራንስፎርም ማድረግ ነው ያሉት ኃላፊው 80 በመቶ የሚሆኑ ጉዳዮች መረጃን መሠረት ያደረጉ ውሳኔዎች/አገልግሎቶች(Data driven decision) እንዲሰጡ ማድረግ ስለሆነ ከወድሁ መንግስት ከአጋር አካላት ጋር ሆነው በነጻ ያቀረበውን ኮደርስ ስልጠና ወስዶ ራስን ብቁ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ኃላፊው ጨምረውም እንደ እንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ 5 ሚልዮን ኮደርስና ሌሎች ዲጂታል ሊትሬሲዎችን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ አቀናጅተን እየሰጠን ነው ብለዋል።
ዲጂታል ዓለም ላይ ተወዳዳሪ ሆኖ መቀጠልና ከዘርፉ የሚገባንን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲሁም በስራ ዓለም ላይ ተወዳዳሪ ሆነው ለመቀጠል መንግስት ያስቀመጠውን እስትራቴጂና መቹ ሁኔታዎች ተጠቅመው የክልላችንን ብሎም የሀገራችንን ብልጽግና እውን እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
