




በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፣ የብልጽግና ፓርቲ የተቋም አደረጃጀት ለማጠናከር የሚያስችል የጽ/ቤት ግንባታ መካሄድ ጀምሯል።
በካፋ ዞን፣ ዴቻ ወረዳ፣ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሀላፊዎች በተገኙበት ባለ ሁለት ወለል የፓርቲ የህንፃ ግንባታ መሠረት ድንጋይ ተቀምጧል።
በመረሃ-ግብር ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን፥ የተቋም ግንባታ በማጠናከር የሀገር መንግሥት ግንባታን ማጽናት ይገባል ብለዋል።
በክልሉ ሁሉም መዋቅሮች የፓርቲ ጽ/ቤት ግንባታ በተደራጀ የአባላትንና ደጋፊዎች ተሳትፎ ለማከናወን መጠነ ሰፊ የዝግጅት ተግባራት ስለመከናወናቸው ያነሱት አቶ ፍቅሬ በዚህም ከ400 ሚሊዮን በላይ ሀብት መሰብሰቡን ተናግረዋል።
ቀጣይ በሁሉም የክልሉ አከባቢዎች የህንፃ ግንባታ የመሠረተ ድንጋይ ተጥሎ ወደ ግንባታ እንደሚገባ ያስታወቁት ሀላፊው በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ለአግልግሎት ዝግጁ እንደሚኾን አስታውቀዋል።
በክልሉ የፓርቲ አደረጃጀትና አሰራር በማጠናከር እንዲሁም በሰው ሀይል በማደራጀት የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በተሟላ መልኩ ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መኾኑን አቶ ፍቅሬ የጠቆሙት።
የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በበኩላቸው ፥ በዞኑ በሚገኙ ሀሉም መዋቅሮች የፓርቲ ቢሮ ግንባታ ወጥ በኾነ መልኩ ለመገንባት በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ጥራት ያለውን የብልጽግና ፓርቲ ቢሮ በመገንባት የተሟላ አግልግሎት ለመስጠት በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት የጀመሩት ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
በወረዳው ለሚገነባው የፓርቲ ህንጻ አባላት ደጋፊዎች ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የገለጹት የዴቻ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወንዱ አደመ፥ የወረዳው ነዋሪዎች በሃሳብ ፣ በገንዘብ እና በቁሳቁስ እያደረጉት ያለው ተሳትፎ መጠናከር አለበት ብለዋል።
በዕለቱ ለህንጻው ግንባታ 50 የደለቡ በሬዎች ስጦታ የተባረከ ሲሆን ግንባታው በፍጥነትና በተሟላ ጥራት በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ቀንና ሌሊት ተሰርቶ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆን እንደሚገባም አቅጣጫ ተቀምጧል።
በዕድገቱ በዛብህ
