







የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የግማሽ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት ያደረገ የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ማስጀመሪያ የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር የማታለም ቸኮል እንደገለጹት፤ የመደመር መንግስት ለከተሞች በሰጠው ልዩ ትኩረት የከተሞች ልማት እንቅስቃሴ እየተነቃቃ ይገኛል።
በ2018 በጀት ዓመት እንደሀገር ለከተማ ልማት ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንዳለም የገለጹት ኢንጂነር የማታለም ቸኮል፤ በክልሉም የከተማ ልማት ሥራዎች እና የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችን ለማሻሻል ሰፊ ሥራዎች እየተከናወነ ይገኛልም ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ ከተሞች ያላቸውን ውስን የከተማ መሬት ሀብቶችን በአግባቡ እንዲያስተዳድሩ፣ ከተሞች በፕላን እንዲመሩ፣ ጽዱና አረንጓዴ እንዲሆኑ እና የከተማ ነዋሪዎች የቤት ባለቤት እንዲሆን በየደረጃው ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።
በመድረኩ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የቦንጋ ከተማ ከንቲባ ዶክተር ተክለአብ ቡሎ መንግስት ከተሞችን ለማዘመን በሚያደረገው እንቅስቃሴ የሁሉም ባለድርሻ ተቋማትና አካላት ሚና መጠናከር ይገባልም ብለዋል።
በመድረኩ የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም እየቀረበ የሚገኝ ሲሆን ከሚቀርበው አፈጻጸም ሪፖርት መነሻ የጋራ ምክክር ተደርገው የቀጣይ አቅጣጫ ይቀመጣል።
በፍቅር ከበደ
