የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የምችል የምርት ሂደት ለተሻለ ገበያ አማራጭ ጉልህ ሚና እንዳለው ተገለጸ

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ግብርና ቢሮ በዘላቂ የመሬት አያያዝ ፕሮግራም የሚደገፉ ተፋሰሶችን ከግል የልማት ህብረቶች (SLMP/RLLP) ጋር በጋራ ለማልማት የአጋርነት ስምምነት መፍጠሪያ አውደ ጥናትና መግባቢያ ስምምነት በቦንጋ ከተማ አካሂዷል።

ይህ ፕሮግራም በሀገር ደረጃ በርካታ ተሞክሮ የተቀመረበት ሲሆን በክልላችን በ3 ዞኖች፣በ6 ወረዳዎች እና በ55 ተፋሰሶች ላይ ከ 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለ 4 ዓመታት የሚተገበር እንደሆነ ተገልፀዋል።

በአውደ ጥናቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አማካሪና ግብርና ቢሮ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ መላኩ:- ክልሉ ለዘላቂ መሬት አያያዝ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልፀው ለዝህም ስኬት የልማት ድርጅቶችና ማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

አቶ የሐንስ ጨምረው ክልላችን በሚታወቀው ቡናና ቅመማ ቀመም ምርት መሬት አያያዝን የሚደግፍ ጥላ ዛፍ በመምረጥ የአዉሮፓ ህብረት ባስቀመጠው መስፈርት ምርቱ የመጣበት ሂደት በማሟላት በተፈጥሯዊነት ቀዳሚ ምርጫ መሆን አለብን ስሉ መልዕክታቸውን አቅርበዋል።

የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩርያ ስምምነቱን ከሰነድ ባሻገር እስካሁን የነበረውን ጅምር ስራ አስፋፍተን 27 የአውሮፓ ሀገራት ባስቀመጡት መመሪያ መሠረት በአካባቢ ጥበቃ መርህ ሳንወጣ የገበያ መዳረሻችንን ማስጠበቅ አለብን ብለዋል።

አቶ አስራት አክለው የማህበረሰባችን ባህል የሆነውን ደን አያያዝ በማጠናከር ከደን ጭፍጨፋ ነፃ የሆነ ምርት በማድረስ እንዲሁም የራሳችን ብራንድ በማውጣት ተፈጥሮ የቸረልንን እምቅ አቅም ልንጠቀም ይገባል ብለዋል።

በክልሉ ግብርና ቢሮ የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮግራም ማናጀር አቶ ናርዶስ ታከለ: ስምምነቱ የግል ድርጅቶች እስካሁን የሠሩትን መልካም ስራ በጥናት አስደግፎ ወደፊት ለማውጣት መሆኑን አብራርተው በመሬት አያያዝ፣ በስራ ዕድል ፈጠራ እና ሰብዓዊ ድጋፍ የተቀናጀ ስራ እንደሚሠራም ገልፀዋል።

የአውደ ጥናቱ ዝርዝር መመርያ በግብርና ሚንስተር የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮግራም ከፍተኛ ኤክስፐርት አቶ ቦጋለ ገላና ቀርበው ሰፊ ማብራርያና ውይይት ተደርገውበታል።

በአውደ ጥናቱ ላይ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው ሁሉም ዜጋና የግሉ ዘርፍ ተፈጥሮን የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አንስተው ህብረተሰቡን በማስተባበር ከአጋር ድርጅቶች ጎን ሆነን የአርሶ አደራችን ተጠቃሚነት ወደ ተሻለ ደረጃ እናደርሳለን ብለዋል።

አውደ ጥናቱን ተከትለው የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ በፕሮግራሙ፣ በግል አልሚ ድርጅቶ እና በተጠቃሚ ወረዳዎች መካካከል ተደርጓል።

በአሻግሬ ገ/ወልድ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *