






በክልሉ በሌማት ትሩፋት ስራዎች የተለዩ 73 መንደሮችን ሞዴል አድርጎ ማሳካት የአመራሩ ቁልፍ ተልዕኮ ሊሆን እንደሚገባ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ተናግረዋል ።
በክልሉ በዘርፉ የተከናወኑ ተግባራትና የቀጣይ አቅጣጫን የሚያመላክት የመወያያ ሰነድ በግብርና ቢሮ ምክል ቢሮ ኃላፊና የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ኃላፊ በሆኑት በአቶ ታመነ በቀለ ቀርቧል።
ተጠናክሮ በቀጠለው የመኸር ግብርና ልማት ስራዎች በሌማት ትሩፋት ስራዎች የእስካሁን አፈጻጸምና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጓል።
አቶ ታመነ በቀለ በሌማት ትሩፋት ስራዎች የተጀመረው ተግባር ውጤታማ እንዲሆን ትኩረት በመስጠት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በሌማት ትሩፋት በክልሉ የተለዩ መንደሮች ስታንዳርዱን እንዲያሟሉ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አቶ ታመነ ተናግረዋል ።
በተከናወኑ ስራዎችም በዓሣ ፣በወተት ፣በስጋ በማር እና በዶሮ ርባታ አዳዲስ መንደሮች መፈጠራቸውና ነባር መንደሮችን ሞዴል የማድረግ ተግባራት የመጡ መሻሻሎች መሆናቸውን አቶ ታመነ ተናግረዋል ።
በእነዚህ ዘርፎችም ከ20 ሺህ በላይ ወጣቶች፣ሴቶችና አርሶአደሮች የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉም ገልጸዋል።
ክልሉ ካለው የተፈጥሮ ጸጋ አንጻር በሌማት ትሩፋት ስራዎች ውጤታማ መሆን የሚያስችል ስነ ምህዳር መኖሩንም አቶ ታመነ ገልጸዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ውይይቱን ባጠቃለሉበት ወቅት እንደተናገሩት የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ በክልሉ ለ5ኛ ጊዜ መሆኑን ተናግረዋል ።
እስካሁን በተደረጉት ንቅናቄዎች በክልሉ ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝም አቶ ማስረሻ በላቸው ተናግረዋል ።
በሌማት ትሩፋት ስራዎች ውጤታማ ለማድረግ የተጀመረውን በመንደር የማደራጀቱ ተግባር አመራሩ ቁርጠኛ ሆኖ ማስፈጸም ይጠበቅበታል ብለዋል።
በውይይቱ የተሳተፉት አካላት የሌማት ትሩፋት ስራዎች ከተጀመሩ ወዲህ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል ።
በዘርፉ ከሚጠበቀው ውጤት አኳያ ግቡ እስኪሳካ ድረስ ተግባሩን በቁርጠኝነት ለማስፈጸም እንደሚጥሩም ተናግረዋል ።
በክልሉ በሌማት ትሩፋት የጀመረውን በመንደር ለይቶ የማብቃት ተግባር እውን ለማድረግ በትብብርና በቅንጅት እንደሚሰሩም ተሳታፊዎች ተናግረዋል ።
የሌማት ትሩፋት ስራዎች በክልሉ አፈጻጸሙ ያለበትን ደረጃ የሚያመላክት የክትትልና ድጋፍ ሪፖርት በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት ወ/ሮ መሠለች ታደመ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
በታጠቅ አበበ
