




ኮርፖሬሽኑ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቦንጋ ከተማ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ ለተገነባውን ቤተ-መጻሕፍት የዲጂታል ላይብራሪ 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር ዋጋ ግምት ያላቸዉን 20 ኮምፒዩተሮችን ድጋፍ አድርጓል።
በመርሀ-ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ኮርፖሬሽኑ የክልሉን ግብርና ለማዘመን የግብርና ግብዓት እና የሜካናይዜሽን አቅርቦት ለማሳለጥ ማዕከል በመገንባት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እያበረከተ ላለው ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
የክልሉ መንግሥት የባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ቤተ-መጻሕፍቱን በቁሳቁስ በማሟላት ለከተማ አስተዳደሩ እንደሚያስረክብ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ሄደት ኮርፖሬሽኑ ያደረገው ድጋፍ የዲጂታል ላይብረሪ ግንባታው የሚደግፍ መኾኑን ተናግረዋል።
ለኮርፖሬሽኑ ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድሩ ሌሎች ተቋማትና ግለሰቦችም ከዚህ ተሞክሮ በመውሰድ ቤተ-መጻሕፍቱን በቁሳቁስ በማሟላት ረገድ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ-አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደ ማርያም በበኩላቸው፥ ኮርፖሬሽኑ የክልሉ ግብርናን ለማዘመን እያደረገ ካለው ዘርፈ-ብዙ ተግባራት ባሻገር የማህበራዊ ልማት ስራዎችን በመደገፍ ለሁለንተናዊ ለውጥ እንደሚተጋ ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥት ለኮርፖሬሽኑ ተግባራት ውጤታማነት እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥል የጠየቁት አቶ ክፍሌ በክልሉ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳደግ ኮርፖሬሽኑ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በርክብክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ የክልሉ የመንግሥት ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
