እንደ ሀገር ያሉብን አምስት ዋና ዋና ችግሮች ተገቢው ቦታ እንዳንደርስ እያደረጉን ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

Spread the love

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደ ሀገር ያሉብን አምስት ዋና ዋና ችግሮች ተገቢው ቦታ እንዳንደርስ እያደረጉን መሆኑን ከንግዱ ማኅበረሰብ ወኪሎች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወረስነው ድህነትና ድህነትን ለመውረስ የተዘጋጀ ትውልድ መኖሩ ከአምስቱ ችግሮቻችን የመጀመሪያው ነው ብለው፤ ድህነትን ወርሰን ለማውረስ ያለን ፍላጎትና መሻት ከፍተኛ መሆኑን በካሳንቺስ በተግባር ታይቷል ሲሉም ገልፀዋል።

ሁለተኛው ችግር እንደሀገር ጠንካራ ተቋም አለመኖር መሆኑን ጠቅሰው፤ ጠዋት የሰጠውን አገልግሎት ከሰዓት መድገም የሚችል ተቋም አለመኖሩ ለዚህ ችግር ማሳያ ነው ብለዋል። ችግሩን ለመፍታት ሪፎርም ሲጀመር በዘርና በኃይማኖት ስም “ታርጋ” የመለጠፍ ባህል በስፋት መታያቱንም ለአብነት አንስተዋል።

ከአራሹ ይልቅ ተኳሹን፤ ከሰራተኛው ይልቅ አጥፊውን የሚያወድስ የአመለካከት ችግር መስተዋሉ ደግሞ ሦስተኛው ችግር መሆኑን ተናግረዋል።

ጀግና ጠዋትና ማታ ሰርቶ ልጆቹን የሚያሳድግ ሳይሆን ክላሽ አንግቶ ሰውን የሚሳደብ ሰው ነው የሚል የተሳሳተ አመለካከት ችግር መኖሩንም ነው ያብራሩት።

አራተኛው ግብርናን በመጀመር ረጅም ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ ከእርሻ ጀማሪዎች መሀል ብትሆንም እስካሁን ምርታማ አለመሆኗ፤ የስልተ ምርት ችግር መኖሩ ማሳያ ነው” ብለዋል። ከችግሩ ለመውጣትም፤ የተሻለ ውጤታማ፣ መሆን የምንችልባቸው መንገዶችን ማሰብና መስራት ይገባል ነው ያሉት።

አምስተኛው የአገልግሎት ችግር ሲሆን፤ “ሥራ ሰርተው ምን ችግር እንዳለበት የማያውቁ፤ አገልግለው የማያውቁ ሰዎች ናቸው ስለ ሥራ የሚናገሩት፤ ይህም የማገልግል ችግር ስለመኖሩ አመላካች ነው” ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚስተወሉ የአመለካከት ችግሮች ካልተፈቱ ሀገራዊ ችግሮችን መፍታት ከባድ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስምረውበታል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *