




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፤በአደጋ ስጋት ስራ አመራር ስርዓት ግንባታና ሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም ግንባታ ትግበራ ማዕቀፎች ዙሪያ የባለድርሻ አካላት የምክር መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን፥ተፈጥሮአዊና ሰው-ሰራሽ አደጋዎችን ተከትሎ የዓለም-አቀፍ ለጋሽ አገሮች የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት በየጊዜው በከፍተኛ ደረጃ እያሽቆለቆለ እንደሚገኝ በመግለጽ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የሰብዓዊ ድጋፍና የፖለቲካ ፍላጐቶች መቆራኘት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህም በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የማኅበራዊ ፍትሕ መጓደል ከማስከተሉ በተጨማሪ የአገርን ክብር፣ ነፃነትና ሉዓላዊነት እየተፈታተነ መምጣቱን በመግለጽ ለዚህም መፍትሄው ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ማሟላት ሲሆን የቤተሰብ ኃላፊነትና የማህበረሰብ አጋርነት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል ብለዋል፡፡
የምንመገበውን የማምረት ያመረትነውን የመመገብ እሳቤን በተግባር በመፈጸም የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ይገባል ያሉት አቶ ፍቅሬ የቤተሰብ ኃላፊነትና የማኅበረሰብ አጋርነትን በማጐልበት የአቅምና የዝግጁነት ጉድለቶችን መቅረፍ ይገባል ብለዋል።
የአደጋ ስጋትና አደጋዎችን በተገቢው መምራትና ማስተዳደር መቻል ዘላቂ የኢኮኖሚ ብልጽግና በማረጋገጥ፤ ማህበራዊ መስተጋብርን በማጠናከርና ፖለቲካዊ መረጋጋትን በማጐልበት አዎንታዊ ሰላምን መገንባት የሚገባ መኾኑን ጠቁመዋል።
አቶ ፍቅሬ አክለው እንደ ክልላችን ያሉን ፀጋዎችን በአግባቡ ተጠቅመን ማህበረሰባዊና ክልላሞ አይበገሬነትን በመረጋገጥ ሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም የመቻል የፓርቲያችን እንሽቲቭ በአግባ በመፈጸም የ2ኛ የአርበኝነት ምዕራፍ ተጋድሎ በአግባቡ መወጣት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በክልሉ የሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም በመቻል ከተረጂነት ወደ ተሟላ አይበገርነት ለመሸጋገር እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ሁሉ አቀፍና በተቀናጀ መንገድ እየተተገበረ እንደሚገኝ ነው የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ለማ መሰለ (ዶ/ር) የገለጹት።
ከቅርብ ተከታታይ አመታት ወዲህ በክልሉ እያጋጠመ ካለዉ አለማቀፉ የአየርንብረት ለውጦች እና በሌሎች ምክንያቶችም አልፎ አልፎ በሚያጋጥሙን ደራሽ የአደጋ ክስተቶች በራስ አቅም ሰፊ ጥረት መደረጉን ነው ዶ/ር ለማ መሰለ የገለጹት።
ባህል ሆኖ የቆየውን ጠባቂነትና የተረጅነት መንፈስ በማስወገድ ሠርተን በሁሉም ቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና የማረጋገጥና የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በብልጽግና ፓርቲ መሪነት የወረዱ ኢንሼትቮች አዎንታዊ ለውጥ እያመጣ መኾኑንም ነው ዶ/ር ለማ ያብራሩት።
በምክክር መድረኩ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸውን ጨምሮ ሌሎች የክልል እና የዞን ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሀላፊዎች እና የባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።
በዕድገቱ በዛብህ
