
በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የተደረሰባቸው ነጥቦች ሙሉ በሙሉ እየተተገበሩ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልፀዋል፡፡
በተለይ የስምምነቱ ዋነኛ ነጥብ የነበረው የመሰረተ ልማት አቅርቦት ጥያቄን መመለስ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም የመሰረተ ልማት አገልግሎቶች፣ የጊዜያዊ አስተዳደር መንግስት የማቋቋም ጥያቄ እና የተፈናቀሉትን የመመለስ ስራዎች ሙሉ በሙሉ እየተተገበሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በራያ፣ በፀለምት እና ሌሎችም አካባቢዎች ተፈናቃዮችን የመመለስ ስራ እየተከናወነ መሆኑን በመግለጽ፤ ይህ ጅምርም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
ስምምነቱ ለነዋሪዎቹ እፎይታ መስጠቱን ገልጸው፤ የሕወኃት አመራሮች ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚፈልጉ እና ከመንግስት ጋር በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ይህን አካሄድ በመቃወም ወደ ኋላ እንድንመለስ የሚፈልጉ አካላት አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህ ተግባራቸው ሊቆጠቡ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡
የፕሪቶሪያው ስምምነት ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ረገድ የባህል ለውጥ ያመጣንበት ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
