












የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት የአምስቱም ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ የ2016 በጀት ዓመት የአስፈጻሚ አካላትን ማጠቃለያ ሪፖርት በታርጫ ከተማ እየገመገመ ይገኛል።
የሪፖርት ግምገማ መድረኩን በንግግር የከፈቱት የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፌጉባኤ ወንድሙ ኩርታ በክልሉ የማሀበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ዕድገት ፋይዳ ያላቸውን ተግባራት አፈጻጸም ተከታትለው መገምገምና ማረም የምክር ቤቱ ተልዕኮ መሆኑን በመግለጽ ከዚህም አኳያ የክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ በበጀት ዓመቱ ውጤታማ ድጋፋዊ ክትትል ማድረጉን ጠቁመዋል።
በየደረጃው ያለው የህዝብ ምክር ቤት የመፈጸምና ማስፈጸም አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ያብራሩት አፌጉባኤ ወንድሙ ኩርታ የክልሉ ምክር ቤት እንደ ተቋም ከቀበሌ ጀምሮ ያሉ የምክር ቤት አደረጃጀት መልሶ የማደራጀትና የማጠናከር ውጤታማ ስራ መስራቱን ተናግረዋል።
የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች የአስፈጻሚ ተቋማት ጠንካራና ደካማ ጎኖች በድጋፋዊ ክትትል በመለየት ለተቋማት ገንቢ ግብረመልስ በየጊዜው እየተሰጠ መምጣቱን የጠቆሙት አፌጉባኤ ወንድሙ የግብረ መልስ አፈጻጸም ክትትል ስረዓት መኖሩንም አስገንዝበዋል።
የየተቋማቱ የበጀት ዓመቱ ዝርዝር የአፈጻጸም ሪፖርት በዘርፉ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች እየተገመገመ የሚገኝ ሲሆን በቀጣይ ከሪፖርቱ መነሻ የጽሁፍ ግብረመልስ ለተቋማቱ እንደሚሰጥም ተገልጿል።
በተግባር አፈጻጸም ግምገማው የአምስቱም ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ የዘርፉ ተቋማት የሥራ ሃላፊዎች እና የቢሮው ማኔጅመንት አባላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በዕድገቱ በዛብህ
