



የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፣ ትምህርት ቢሮ 2ተኛውን የትምህርት አስተዳደር ጉባኤ በታርጫ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።
በጉባኤው ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፥ በክልሉ የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻል በተሰጠው ትኩረት መሻሻሎች እየታዩ መኾኑን ተናግረዋል።
በማኅበረሰብ ተሳትፎ የትምህርት ቤት ደረጃ ማሻሻልና የትምህርት ግብዓት ከማሟላት አኳያ አበረታች ውጤት መመዝገቡን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በተያዘው በጀት ዓመትም ይህንን ተግባር አጠናክረው ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
የመምህራን ልማትና አቅም ግንባታ ተግባራት መጠናከር እንዳለበት ያስገነዘቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በተለይም በከተሞች ለመምህራን የጋራ መኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እንዲመቻችላቸው አሳስበዋል።
በትምህርት ዘርፍ የሚጠበቀውን ውጤት ለማስመዝገብ የባለድርሻ አካላት ቅንጅትና ትብብር መጠናከር አለበት ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የትምህርት ልማት ሥራዎችን ከገጠር ትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎች ጋር በማስተሳሰር በላቀ ውጤት መፈጸም ይገባል ብለዋል።
በክልሉ የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻልና የፈተና ምዘና ሥርዓት ለማዘመን በተከናወኑ ስራዎች ውጤት መመዝገቡን ነው በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ የገለጹት።
የትምህርት ባለድርሻ አካላት፥ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ ቁርጠኛ በመኾን የትምህርት ለትውልድን ማጠናከር፣ የትምህርት አመራር ስምርትና ተጠያቂነት ማስፈን፣ የውጤት ማሻሻያ ተግባራትን ማጠናከር እንዲሁም የትምህርት ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማሳደግ ይገባል ብለዋል አቶ አልማው።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንሼቲቭ የኾነው የሞዴል ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ በጥሩ አፈጻጸም እየተከናወነ ነው ያሉት አቶ አልማው፥ እንደ አጠቃላይ በትምህርት ዘርፍ የተጀማመሩ መልካም ተሞክሮዎችን በማስቀጠል የትምህርት ስብራትን በዘላቂነት መጠገን እንደሚገባ ተናግረዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
