የአርሶ አደር መስክ ትምህርት ቤቱ ችግርን በራስ አቅም ለመፍታት እንዳገዛቸው አርሶ አደሮችና ተሳታፊዎች ገለጹ

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ተሳትፏዊ ግብርናና የአየር ንብረት ሽግግር (PACT) ፕሮግራም ድጋፍ በምዕራብ ኦሞ ዞን በማጂ ወረዳ አኩ የመሬት ገጽታ (Land scape) በኑቹ አርሶ አደር መስክ ትምህርት ቤት የመስክ ልምድ ልውውጥ ተካሂደዋል።

በአርሶ-አደሮች መካከል የልምድ ልውውጥ መፍጠር ለተሻለ ምርታማነት እንደሚያበቃ ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።

የአርሶ አደር መስክ ትምህርት ቤት በአነስተኛ ማሳ ትምህርት የሚወስዱበት፣ በአካል የተሻለውን ለመወሰንና ቴክኖሎጂን ለመምረጥ አቅምና ዕድል የሚያገኝበት መሆኑን ተሳታፊዎቹ አክለዋል።

የቀበሌ ግብርና ባለሙያዋ ባር ኘንግ ከዚህ በፊት በአካባቢው የስንዴ ምርታማነት እየቀነሰ መምጣቱን በማስታወስ ምርምሩ የተሻለውን በመምረጥ ችግሩን ለመፍታት እንዳገዛቸው አንስተዋል።

የኑቹ አርሶ አደር መስክ ትምህርት ቤት የአንድ ቡድን ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ተፈራ ወንድሙ በአነስተኛ ማሳ በንጽጽር ከተሰራው ውጤታማ የሆነውን በራስ አቅም መለየት መቻሉን በመግለፅ ያገኙትን ዕውቀት ወደ ግል ማሳ በመውሰድ ተጠቃሚ ለመሆን ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።

በቡድን ከተደራጁ አርሶ አደሮች አቶ ቻም ዱርና እና ወ/ሮ ወርቅን ያንግ በመስክ ት/ቤቱ የተገኘው ውጤት ያለ ቴክኖሎጂ በማምረት ምርታማነቱ ከሚንስበት በመውጣት ቴክኖሎጅን በመጠቀም በሙሉ ፓኬጅ በማልማት የተሻለ ውጤት ለማግኘት እንዳነሳሳቸው ገልጸዋል።

ከዳውሮ ዞን ሎማ ቦሳ ወረዳ የመጡት አቶ ደነቀ ኡማ አካባቢውን በማየታቸው መደሰታቸውን በመግለጽ በንጽጽር ከለማው ማሳ በሙሉ ፓኬጅን ተጠቅመው የዘሩት ስንዴ ውጤታማ መሆኑን ገልጸው ይህን ወደ አካባቢው ወስዶ ለማስተማር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አቶ ታርኩ መሰና ከዳውሮ ዞን ከጌና ወረዳ ተሳታፊ ሲሆን የመስክ ምልከታው የልምድ ልውውጥ በማድረግና በመማማር የተሻለ ውጤት ለማምጣት ያስችላል ብለዋል፡፡

በስርዓተ ጾታ በተሰጠው ስልጠና የሞደል ቤተሰብ በአስተሳሰብና በተግባር ለውጥ በማምጣት የሴቶችን ስራ ጫና ከመቀነስም በላይ የፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ምቹ መደላደል እየፈጠረ መምጣቱን የገለጹት በግብርና ቢሮ የስርዓተ ጾታ ኤክስፐርት የሆኑት ወ/ሮ ሮዛ ቃሲም ናቸው።

በልምድ ልውውጡ የታዩ ስራዎችን በሌሎች አካባቢዎች ማስፋፋት እንደሚገባ ተሳታፊዎች አመላክተዋል።

በጌታሁን ግርማ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *