የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና በዲጂታሉ አለም ክህሎት ያለው ዜጋ ለመፍጠር ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተጠቆመ።

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር ለዳውሮ ዞን ታርጫ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በኢትዮ-ኮደርስ ስልጠናና ዲጂታል መታወቂያ ዙሪያ ግንዛቤ አስጨብጧል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትልና የስራ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አባተ ኡቃ ከ6ኛ ክፍል ጀምሮ ያሉ ተማሪዎች ዲጂታል መታወቂያ ሊኖራቸው እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡን ጠቁመው፤በተለይ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ለብሄራዊ ፈተና መታወቂያው ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።

መታወቂያው እንደ ሀገር የዜጎችን መረጃ በመያዝ በቂ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችልም ተመላክቷል።

የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ ኃላፊ ረ/ኘሮፌሰር ዘመድኩን ሰለሞን በበኩላቸው የስልጠናው አላማ በ3 ተከታታይ አመታት 5 ሚሊየን ዜጎችን በመሠረታዊ ዲጂታል ክህሎት አሰልጥኖ እውቅና መስጠት ነው ብለዋል።

ስልጠናው በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ(ዶ/ር) አነሳሽነትና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ድጋፍ እየተሰጠ ሲሆን፤ስልጠናውን ሲያጠናቅቁ በአለምአቀፍ ገበያ ስራ የሚያገኙበትን አማራጭ ለመፍጠር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ዩዳሲቲ የሚባል ኘላትፎርም ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በ4 ክህሎቶች ማለትም በአርተፊሻል ኢንተሊጀንስ፣ዳታ ሳይንስ፣ኘሮግራሚንግና በአንድሮይድ ዙሪያ ስልጠናውን ለመስጠት ስምምነት አድርገዋል።

እንደ ክልል በሶስት አመት 138 ሺ የሚሆኑ ዜጎችን ለማሰልጠን መታቀዱን የተናገሩት የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስፋው በክልሉ ከ13 አመት በላይ የሆኑ ኢትዮጲያዊን ዲጂታል መታወቂያ እንዲያገኙ በቢሮው ግብ አድርገው እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሰልጣኞች ከክልሉ 6ቱም ዞኖች የህዝብ ቁጥር ታይቶ በኮታ የሚወሰዱ ሲሆን ሁሉም የባለድርሻ አካላት ቅስቀሳ ማድረግ ጀምረዋል ሲል የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *