በከተማው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሻሻል በተሰጠው ትኩረት አዎንታዊ ለውጥ መመዝገቡ ተገለጸ

Spread the love

በዳውሮ ዞን፣ ታርጫ ከተማ የሚስተዋለውን ስር የሰደደ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሻሻል የባለድርሻ አካላት በሰጡት ትኩረት አውንታዊ ለውጥ መመዝገቡን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

የታርጫ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዳዊት ወንድሙ፥ የዞኑ ዋና ከተማና የክልሉ ብዝሀ ማዕከል በሆነችሁ የታርጫ ከተማ የሚስተዋለውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በዘላቂነት ለማሻሻል የክልሉ መንግሥት ሌሎች የባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ባደረገው ርብርብ አሁን ላይ የከተማው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በተጨባጭ ለውጥ ማሳየቱን አብራርተዋል።

በከተማው ያለውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ውስንነት ለመቅረፍ ከአለምአቀፍ አበዳሪ ተቋማት እና በየደረጃው ከሚገኘው የመንግሥት መዋቅር በወጪ መጋራት ስርዓት በተገኘው ሀብት ግንባታው ተከናውኖ በቅርቡ ወደ አገልግሎት የገባው የታርጫ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት፥ የከተማውን የውሃ ችግር ትርጉም ባለው መልኩ የፈታ መሆኑን ነው አቶ ዳዊት ያስረዱት።

የከተማ አስተዳደሩ የውሃ አግልግሎት ጽ/ቤት ስራ-አስኪያጅ አቶ አብነት ቸርነት በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ወደ ስራ በመግባቱ የከተማው የውሃ ሽፋን ቀድሞ ከነበረበት አሁን ላይ 85 ከመቶ መድረሱን ተናግረዋል።

በዚህም በከተማው ህብረተሰብ ዘንድ ዘወትር የሚነሳውን የውሃ ፍላጎት ከወትሮው በተሻለ ሁኔታ መመለስ መቻሉን የገለጹት አቶ አብነት ይሁን እንጂ በነባር የውሃ መስመሮች አልፎ አልፎ በሚፈጠረው ጊዜያዊ ችግሮች በአንዳንድ የከተማው አከባቢዎች የሚከሰተውን የአጭር ጊዜ የውሃ አቅርቦት መዘግየትን በዘላቂነት ለማሻሻል መስሪያ ቤቱ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የከተማው ነዋሪ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚጨምር እንደሆነና የከርሰምድር ውሃ ይዞታ በባህርይው የሚዋዥቅ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው ለከተማው ተጨማሪ የውሃ አቅርቦት ለማስፋት የከተማ አስተዳደሩ፣ ከዞን እና ከክልል ጋር በመቀናጀት የተጨማሪ ጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ እና በፕሮጀክት የምንጭ ማጎልበት ተግባር እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም በክልሉ መንግሥት ድጋፍ ተጨማሪ የጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ የተከናወነ ሲሆን በቀጣይ አጭር ጊዜያት ግንባታው ተጠናቆ ለዋናው መስመር መጋቢ እንደሚሆን የገለጹት አቶ አብነት ከዚህ በተጨማሪ የከተማውን የንጹህ ውሃ አቅርቦት በማሻሻል የታርጫ ከተማን ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ ‘ዊንጊስ አፕ ሂሊንግ’ የተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅትን በማስተባበር የምንጭ ማጎልበት ስራ መከናወኑንና በዚህም ህብረተሰቡ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል።

የ’ዊንጊስ አፕ ሂሊንግ’ ውሃ ለጤና ፕሮጀክት አስተባባሪ ኢንጂነር ሳምሶን በኩ እንደገለጹት ድርጅቱ በዞኑ የውሃ ችግር ባለባቸው አከባቢዎች በውሃ ምንጭ ማጎልበትና ቦኖ ግንባታ ባለፋት ሶስት ዓመታት በርካታ ተግባራትን አከናውኗል።

ፕሮጀክቱ በተላይ በታርጫ ከተማ ያለውን መጠነ ሰፊ የውሃ ችግር ለመቅረፍ በከተማ አስተዳደሩ ጋር በመቀናጀት በሶስት የከተማው ክፍል ምንጭ በማጎልበት ዘላቂ ፍሰት ያለውን ውሃ እያቀረበ መሆኑን የገለጹት ኢንጅነር ሳምሶን ህብረተሰቡ የተገነቡ የውሃ አውታሮች ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጡ በባለቤትነት መጠበቅና ማስተዳደር እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።

የታርጫ ከተማ 02 ነዋሪ ከሆኑት መካከል አቶ ያዕቆብ አምቦማ እና ወ/ሮ አሜሪካን ጋምበሮ በከተማው የንጹህ ውሃ አቅርቦት ችግር በመኖሩ ከዚህ በፊት አንድ ጊዜ የተቀዳውን ውሃ ለወራት ለመጠቀም እንደሚገደዱ በመግለጽ ይሁን እንጅ አሁን ላይ መንግሥት ከረጂ የልማት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ይህንን ችግር ለመፍታት በሰሩት የሚመሰገን ተግባር ንጹሕ ውሃን በቀናት ልዩነት ማግኘት መቻሉን በማንሳት በዚህም የራሳቸውንና የቤተሰቦቻቸውን ጤና መጠበቅ እንደተቻለ አስረድተዋል።

በከተማው የአረንጓዴ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት አበባ ፋልታሞ እንደገለጹት በትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በመዘርጋቱ በመማር ማስተማር ስራ ላይ አውንታዊ ለውጥ ተመዝግቧል።

በዚህም ተማሪዎች ውሃ ስጠማቸው ንጹሕ ውሃ በቅርበት እያገኙ፣ ሙቀት ስሰማቸው በነጻነት እየታጠቡ እንዲሁም በቂ የውሃ አቅርቦት በመኖሩ የመማሪያ ክፍሎች ንጽሕናቸውን በተገቢው በመጠበቅ ለመማር ማስተማር ስራ ምቹ በማድረግ ጤንነታቸው የተጠበቁ ዜጎች በእውቀት ማነጽ እየተቻለ መሆኑን አስረድተዋል።

በአጠቃላይ በከተማው የነበረውን አንገብጋቢ የውሃ ችግር ለመፍታት የክልሉ መንግስት በየደረጃው ህብረተሰቡንና ሌሎች የባለድርሻ አካላትን በማቀናጀት በሰጠው ትኩረት ለተገኘው አዎንታዊ ውጤት ምስጋና ያቀረቡት የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ዳዊት ወንድሙ ህብረተሰቡ የውሃ መሠረተ ልማቶችን በእኔነት ስሜት በመጠበቅ ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *