





ያለ አግባብ የሚባክነውን የህዝብ ሀብት ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ማድረግ ይገባል ሲሉ አፈጉባኤ ወንድሙ ኩርታ ተናግረዋል ።
በኦዲት ግኝት አመላለስ ፣የፋይናንስ አስተዳደር እና ሂሳብ አያያዝ ዙሪያ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ እያደረገ ነው።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ምክርቤት ዋና አፈጉባዔ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ የህዝብ ሀብት ከብክነት ለመታደግ ለታለመለት ዓላማ ብቻ እንዲውል መደረግ አለበት ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት በክልሉ የመንግስት እና የህዝብ ሀብትን በመስረቅና በማጭበርበር የተሳተፉ አካላትን ወደ ህግ በማቅረብ ተጠያቂነትን ማስፈን ይገባል ሲሉም ተናግረዋል ።
የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ በበኩላቸው የሂሳብ አያያዝና አወቃቀርን ያልተከተለ የበጀት ምዝገባ ፣ ተቀባይነት ያላላቸውን አሰራሮች አለመከተል፣የሂሳብ አያያዝ መርህን አለመከተል ለሀብት ብክነት መነሻ የሆኑ የአሰራር ክፍተቶች መሆናቸውን አመላክተዋል።
የመንግስት እና የህዝብ ሀብት ብክነትን ለመከላከል የውስጥ ቁጥጥር ስርዓት ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች መከናወን ይኖርበታል ሲሉም ወ/ሮ ወሰነች ተናግረዋል ።
ለዚህም ውጤታማነት የህግና ፍትህ አካላት እንዲሁም ተሳታፊ ባለድርሻ አካላት የኦዲት ግኝት ሪፖርትን መሠረት በማድረግ የባከኑ ሀብቶችን የማስመለስና አጥፊዎች በህግ የሚጠየቁበት ሁኔታ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
በክልሉ በኦዲት ግኝት አፈጻጸም የምክክር መድረክ የክልሉ ኦዲት ግኝት አስመላሽ ግብረሀይል የ6ቱ ዞን ዋና አፈ ጉባዔዎች ፣ የፋይናንስ መምሪያ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል ።
በታጠቅ አበበ
